ትንቢተ ኢሳይያስ 49:14-26

ትንቢተ ኢሳይያስ 49:14-26 መቅካእኤ

ጽዮን ግን፦ “ጌታ ትቶኛል፥ እርሱ ረስቶኛል” አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ የተወለደው ሕጻን ልጇን ትረሳለች? ርህራሄ አልባስ እስክመሆን ትደርሳለች? አዎን፥ እርሷ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ። ልጆችሽ ይፈጥናሉ፥ ሊያፈረሱሽና ሊያወደሙሽ ከአንቺ ይወጣሉ። ዓይንሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል ጌታ። ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተነሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉ። የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ፦ “ስፍራ ጠብቦኛልና እድንቀመጥ ቦታ አስፊልን” ይላሉ። አንቺም በልብሽ፦ “የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁ፥ ተቅበዝብዤአለሁ፥ እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ?” ትያለሽ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓላማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በዕቅፋቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዝቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ፤ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም። በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይነጠቃል? ወይስ ከጨካኙ ምርኮኞችን ማስመለጥ ይቻላል? ጌታ ግን እንዲህ ይላል፦ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁና፥ በኃያላን የተማረኩ እንኳን ይወሰዳሉ፥ የጨካኞች ብዝበዛም ቢሆን ያመልጣል። አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሠክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ ጌታ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደሆንሁ ያውቃል።