የኢየሩሳሌም ሕዝብ ግን፥ “እግዚአብሔር ትቶናል፤ ጌታዬም ረስቶናል” አሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልሳል፦ “እናት የምታጠባውን ልጅዋን ልትረሳ ትችላለችን? ወይስ ለወለደችው ልጅ አትራራምን? እርስዋ እንኳ ብትረሳ እኔ ግን እናንተን አልረሳም። ኢየሩሳሌም ሆይ! እነሆ፥ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤ ቅጥሮችሽንም ዘወትር አስታውሳለሁ። “አንቺን የሚገነቡ ፈጣኖች ናቸው፤ ያወደሙሽ ግን ከአንቺ ርቀው ይሄዳሉ። ቀና ብለሽ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤ ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ እንዲህ እላለሁ፦ ‘ሁሉንም እንደ ልብስ ትለብሺአቸዋለሽ፤ ሙሽራ በጌጣጌጥ እንደምታጌጥ አንቺም በእነርሱ ታጌጪአለሽ።’ “ ‘ፈራርሰሽ ባድማ እንድትሆኚ፥ ምድርሽም ጠፍ እንዲሆን ቢያደርጉሽም እንኳ፥ አሁን አንቺ ተመልሰው ለሚመጡ ለነዋሪዎችሽ ጠባብ ትሆኚአለሽ፤ የአፈራረሱሽም ከአንቺ ርቀው ይሄዳሉ።’ በስደት የተወለዱ ልጆችሽ ‘ይህ ቦታ ለእኛ በጣም ጠባብ ስለ ሆነ የምንኖርበት ሰፊ ቦታ ስጪን’ ይሉሻል። ከዚህ በኋላ አንቺም በልብሽ እንዲህ ትያለሽ፦ ‘እነዚህን ልጆች ማን ወለደልኝ? ብዙ ልጆቼን አጥቼና የወላድ መኻን ሆኜ ነበር፤ ተሰድጄ፥ ተቀባይነትም አጥቼ ነበር፤ ታዲያ እነዚህን ልጆች ያሳደጋቸው ማነው? እኔ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እንግዲህ እነዚህ ልጆች ከወዴት መጡ?’ ” ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወንዶች ልጆችሽን በክንዳቸው፥ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ተሸክመው ያመጡ ዘንድ ለመንግሥታት ምልክት እሰጣለሁ፤ ለሕዝቦችም ዐርማን አነሣለሁ። ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል። የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂአለሽ፤ የእኔን ርዳታ ለማግኘት የሚጠባበቁ ከቶ አያፍሩም።” ከጀግና እጅ ምርኮን መውሰድ ይቻላልን? ወይስ ከጨካኝ ሰው እጅ ምርኮኛን ማስለቀቅ ይቻላልን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ “አንቺን የሚቃወሙሽን እኔ ስለምቃወም፥ ጀግና የያዘው ምርኮኛ እንኳ ይወሰዳል፤ ከጨካኝ እጅም ምርኮ ይለቀቃል፤ እኔም ልጆችሽን አድናለሁ። ጨቋኞችሽ የገዛ ሥጋቸውን እንዲበሉ አደርጋለሁ፤ በወይን ጠጅ እንደሚሰክሩ የገዛ ደማቸውን ጠጥተው እንዲሰክሩ አደርጋለሁ። ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ የእስራኤል ኀያል አምላክ መሆኔን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ያውቃል።”
ትንቢተ ኢሳይያስ 49 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 49:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች