ጽዮን ግን፥ “እግዚአብሔር ትቶኛል፤ ጌታም ረስቶኛል” አለች። “በውኑ ሴት፥ ልጅዋን ትረሳለችን? ከማኅፀንዋ ለተወለደውስ አትራራምን? ሴት ይህን ብትረሳ፥ እኔ አንቺን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ ግንቦችሽን ሣልሁ፤ አንቺም ሁልጊዜ በፊቴ ነሽ። ከአፈረሱሽ በኋላ ፈጥነሽ ትታነጺያለሽ፤ ያፈረሱሽ ከአንቺ ይወጣሉ። ዐይንሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊአቸዋለሽ ይላል እግዚአብሔር። ፈርሰሻልና፥ ፈጽመሽም ጠፍተሻልና በአንቺ ለሚኖሩ ሰዎች ዛሬ ጠባብ ትሆኚባቸዋለሽ፤ ያጠፉሽም ከአንቺ ይርቃሉ። አጥተሻቸው የነበሩት ልጆችሽም በጆሮሽ፦ ስፍራ ጠብቦናልና የምንቀመጥበት ቦታ አስፊልን ይላሉ። አንቺም በልብሽ፦ የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም መበለት ነኝና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ከወዴት መጡ?” ትያለሽ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፤ ዓርማዬንም ወደ ደሴቶች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ታቅፈው ያመጡአቸዋል፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። ነገሥታትም አሳዳጊዎች አባቶችሽ ይሆናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም።” በውኑ ምርኮን ከኀይለኛ እጅ መቀማት ይቻላልን? በግፍ የተማረከስ ይድናልን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፥ “በኀያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፤ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፤ እኔም ፍርድሽን እፈርድልሻለሁ፤ ልጆችሽንም አድናለሁ። የአስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን ይበላሉ፤ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅም ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኀኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብን ኀይል የምደግፍ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
ትንቢተ ኢሳይያስ 49 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 49:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች