እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፥ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፥ በእውነት ፍርድን ያወጣል። በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፥ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለህ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ስሜ ይህ ነው፥ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፥ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፥ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፥ ምሥጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፥ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፥ አሁን ምጥ እንደያዛት ሴት እጮኻለሁ፥ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፥ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኵሬዎችንም አደርቃለሁ። ዕውሮችንም በማያቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፥ በማያቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፥ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውምም። በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፦ አምላኮቻችን ናችሁ የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ።
ትንቢተ ኢሳይያስ 42 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 42:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች