ኢሳይያስ 42:1-17
ኢሳይያስ 42:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነሆ፥ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ ያዕቆብ፤ ነፍሴ የተቀበለችው ምርጤ እስራኤልም፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያመጣል። አይጮኽም፤ ቃሉንም አያነሣም፤ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ ነገር ግን በእውነት ፍርድን ያመጣል። በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። ሰማይን የፈጠረ፥ የዘረጋውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ሁሉ ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ በእጄም እይዝሃለሁ፤ አበረታሃለሁም፤ ለልጅ ልጅ ቃል ኪዳን፥ ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። የዕውራንንም ዐይን ትከፍት ዘንድ፥ የተጋዙትንም ከግዞት ቤት፥ በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ። እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፤ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይነገር እርሱን አስታውቃችኋለሁ።” ወደ ባሕር የምትወርዱ፥ በእርስዋም ውስጥ የምትጓዙ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ ከምድርም ዳርቻ ስሙን አክብሩ። ምድረ በዳውና ከተሞችዋ፥ የቄዳርም ነዋሪዎችና መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በዋሻም የሚኖሩ እልል ይበሉ፤ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ኀይለኛውንም ያጠፋል፤ ቅንአትንም ያስነሣል፤ በጠላቶቹም ላይ በኀይል ይጮኻል። ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፤ እንግዲህ ለዘለዓለም ዝም እላለሁን? አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እታገሣለሁ፤ አጠፋለሁ፤ በአንድነትም እጨርሳለሁ። ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፤ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፤ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ የማያውቋትንም ጎዳና እንዲረግጡ አደርጋቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ አልተዋቸውምም። በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፥ “አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመውም ያፍራሉ።
ኢሳይያስ 42:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እነሆ፤ ደግፌ የያዝሁት፣ በርሱም ደስ የሚለኝ የመረጥሁት አገልጋዬ፤ መንፈሴን በርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል። አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል። ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣ አይደክምም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።” ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣ ለሕዝቧ እስትንፋስን፣ ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ። የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ። “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው! ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም። እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሟል፤ እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ፤ ከመብቀሉም በፊት፣ ለእናንተ አስታውቃለሁ።” እግዚአብሔር እናንተ ወደ ባሕር የምትወርዱ፣ በዚያም ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በዚያ የምትኖሩ በሙሉ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድር ዳርቻም ምስጋናውን ዘምሩ። ምድረ በዳውና ከተሞቹ ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤ ቄዳር ያለችበት መንደር ደስ ይበለው፤ የሴላ ሕዝቦች በደስታ ይዘምሩ፤ ከተራሮችም ራስ ላይ ይጩኹ። ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ። እግዚአብሔር እንደ ኀያል ሰው ይዘምታል፤ እንደ ተዋጊ በቅናት ይነሣል፤ የቀረርቶ ጩኸት ያሰማል፤ ጠላቶቹንም ድል ያደርጋል። “ለረዥም ጊዜ ዝም አልሁ፤ ጸጥ አልሁ፤ ራሴንም ገታሁ፤ አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣ እጮኻለሁ፤ ቍና ቍና እቃትታለሁ፤ እተነፍሳለሁ። ተራራውንና ኰረብታውን አፈርሳለሁ፤ ዕፀዋቱን ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዙንም ደሴት አደርጋለሁ፤ ኵሬውን አደርቃለሁ። ዕውሮችን በማያወቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ። ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ። ይህን አደርጋለሁ፤ አልተዋቸውም። በጣዖት የሚታመኑ ግን፣ ምስሎችን፣ ‘አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ፣ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመው ይዋረዳሉም።
ኢሳይያስ 42:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፥ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፥ በእውነት ፍርድን ያወጣል። በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፥ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለህ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ስሜ ይህ ነው፥ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፥ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፥ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፥ ምሥጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፥ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፥ አሁን ምጥ እንደያዛት ሴት እጮኻለሁ፥ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፥ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኵሬዎችንም አደርቃለሁ። ዕውሮችንም በማያቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፥ በማያቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፥ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውምም። በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፦ አምላኮቻችን ናችሁ የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ።
ኢሳይያስ 42:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምደግፈው የመረጥኩትና በእርሱም ደስ የሚለኝ አገልጋዬ ይህ ነው፤ መንፈሴ በእርሱ እንዲያድርበት አደርጋለሁ፤ እርሱ ለሕዝቦች ሁሉ ትክክለኛ ፍርድን ያመጣል። ጮኾ አይናገርም፤ ድምጡንም በየአደባባዩ እንዲሰማ አያደርግም። የተቀጠቀጠ ሸምበቆን እንኳ አይሰብርም፤ ሊጠፋ የተቃረበውንም መብራት አያጠፋም፤ በታማኝነት ፍትሕን ያስገኛል። በምድር ላይ ፍትሕን እስኪመሠርት ድረስ እርሱ አይታክትም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ በሩቅ ያሉ ሕዝቦችም የእርሱን ትምህርት ለመስማት ይናፍቃሉ።” ሰማይን የፈጠረና ከዳር እስከ ዳር የዘረጋው፥ ምድርንና በውስጥዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሠራ፥ ሕይወትንና እስትንፋስንም የሰጣቸው፥ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህን ይዤ ጠብቄሃለሁ፤ ለወገኖቼ እንደ ቃል ኪዳን፥ ለአሕዛብ እንደ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ። ስለዚህ የዕውሮችን ዐይን ታበራለህ፤ በጨለማው ጒድጓድ እስር ቤት ውስጥ ያሉትን እስረኞችን ታወጣለህ። “ስሜ እግዚአብሔር ነው፤ የእኔንም ክብር የሚጋራ ሌላ አምላክ የለም፤ ጣዖቶችም ምስጋናዬን እንዲካፈሉ አልፈቅድም። እነሆ፥ እኔ አስቀድሜ የተናገርኳቸው ነገሮች ሁሉ ተፈጽመዋል፤ አሁን ደግሞ ወደ ፊት ስለሚሆኑት አዳዲስ ነገሮች፥ ከመፈጸማቸው በፊት እናገራለሁ።” ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ! የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የምስጋና መዝሙር አቅርቡ! በባሕሩ ውስጥ ያሉት ሁሉ፥ የጠረፍ አገሮችና በእነርሱም የሚኖሩ ሁሉ ያመስግኑ! በረሓና በበረሓ የሚገኙ ከተሞች፦ እንዲሁም የቄዳር ሕዝቦች የሚኖሩባት መንደር ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤ የሴላዕ ከተማ ነዋሪዎች በደስታ ይዘምሩ፤ ከተራሮችም ጫፍ የእልልታ ድምፅ ያሰሙ። እነርሱም እግዚአብሔርን ያክብሩ፤ በጠረፍ አገሮችም ላይ ምስጋናውን ያውጁ። እግዚአብሔር እንደ ጀግና ወታደር ይወጣል፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ ጦርነትን ያውጃል፤ በጠላቶቹም ላይ ድልን ይጐናጸፋል። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለረጅም ጊዜ ታገሥኩ፤ ጸጥ ብዬም ራሴን ገታሁ፤ አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት ከፍተኛ ድምፅ አሰማለሁ፤ የቊጣ እስትንፋስ እተነፍሳለሁ። ተራራዎችንና ኰረብቶችን አጠፋለሁ፤ በእነርሱ ላይ የበቀሉትን ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችን ወደ ደረቅ ምድር እለውጣለሁ፤ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። “ዕውሮችን ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ቀድሞ ባላወቁትም መንገድ እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸው የተጋረደውንም ጨለማ ወደ ብርሃንነት እለውጣለሁ፤ ወጣገባ የሆነውንም ስፍራ አስተካክላለሁ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እኔ የምፈጽማቸው ናቸው፤ አልተዋቸውምም። በጣዖቶች ተማምነው ምስሎችን ‘እናንተ አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ ኀፍረት ይደርስባቸዋል።”
ኢሳይያስ 42:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል። በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፤ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ። የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፤ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ። እኔ ጌታ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርሷም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ፥ ለጌታ አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለጌታ ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። ጌታ እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። ዕውሮችንም በማያውቁት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ በማያውቁትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውም። በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፦ “አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ።