ትንቢተ ኢሳይያስ 42:1-17

ትንቢተ ኢሳይያስ 42:1-17 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምደግፈው የመረጥኩትና በእርሱም ደስ የሚለኝ አገልጋዬ ይህ ነው፤ መንፈሴ በእርሱ እንዲያድርበት አደርጋለሁ፤ እርሱ ለሕዝቦች ሁሉ ትክክለኛ ፍርድን ያመጣል። ጮኾ አይናገርም፤ ድምጡንም በየአደባባዩ እንዲሰማ አያደርግም። የተቀጠቀጠ ሸምበቆን እንኳ አይሰብርም፤ ሊጠፋ የተቃረበውንም መብራት አያጠፋም፤ በታማኝነት ፍትሕን ያስገኛል። በምድር ላይ ፍትሕን እስኪመሠርት ድረስ እርሱ አይታክትም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ በሩቅ ያሉ ሕዝቦችም የእርሱን ትምህርት ለመስማት ይናፍቃሉ።” ሰማይን የፈጠረና ከዳር እስከ ዳር የዘረጋው፥ ምድርንና በውስጥዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሠራ፥ ሕይወትንና እስትንፋስንም የሰጣቸው፥ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህን ይዤ ጠብቄሃለሁ፤ ለወገኖቼ እንደ ቃል ኪዳን፥ ለአሕዛብ እንደ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ። ስለዚህ የዕውሮችን ዐይን ታበራለህ፤ በጨለማው ጒድጓድ እስር ቤት ውስጥ ያሉትን እስረኞችን ታወጣለህ። “ስሜ እግዚአብሔር ነው፤ የእኔንም ክብር የሚጋራ ሌላ አምላክ የለም፤ ጣዖቶችም ምስጋናዬን እንዲካፈሉ አልፈቅድም። እነሆ፥ እኔ አስቀድሜ የተናገርኳቸው ነገሮች ሁሉ ተፈጽመዋል፤ አሁን ደግሞ ወደ ፊት ስለሚሆኑት አዳዲስ ነገሮች፥ ከመፈጸማቸው በፊት እናገራለሁ።” ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ! የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የምስጋና መዝሙር አቅርቡ! በባሕሩ ውስጥ ያሉት ሁሉ፥ የጠረፍ አገሮችና በእነርሱም የሚኖሩ ሁሉ ያመስግኑ! በረሓና በበረሓ የሚገኙ ከተሞች፦ እንዲሁም የቄዳር ሕዝቦች የሚኖሩባት መንደር ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤ የሴላዕ ከተማ ነዋሪዎች በደስታ ይዘምሩ፤ ከተራሮችም ጫፍ የእልልታ ድምፅ ያሰሙ። እነርሱም እግዚአብሔርን ያክብሩ፤ በጠረፍ አገሮችም ላይ ምስጋናውን ያውጁ። እግዚአብሔር እንደ ጀግና ወታደር ይወጣል፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ ጦርነትን ያውጃል፤ በጠላቶቹም ላይ ድልን ይጐናጸፋል። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለረጅም ጊዜ ታገሥኩ፤ ጸጥ ብዬም ራሴን ገታሁ፤ አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት ከፍተኛ ድምፅ አሰማለሁ፤ የቊጣ እስትንፋስ እተነፍሳለሁ። ተራራዎችንና ኰረብቶችን አጠፋለሁ፤ በእነርሱ ላይ የበቀሉትን ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችን ወደ ደረቅ ምድር እለውጣለሁ፤ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። “ዕውሮችን ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ቀድሞ ባላወቁትም መንገድ እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸው የተጋረደውንም ጨለማ ወደ ብርሃንነት እለውጣለሁ፤ ወጣገባ የሆነውንም ስፍራ አስተካክላለሁ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እኔ የምፈጽማቸው ናቸው፤ አልተዋቸውምም። በጣዖቶች ተማምነው ምስሎችን ‘እናንተ አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ ኀፍረት ይደርስባቸዋል።”