መጽሐፈ ዮዲት 13

13
1በመሸም ጊዜ ባርያዎቹ ተጣድፈው ወጡ፤ ባጎስም ድንኳኑን ከውጭ ዘጋ፥ በጌታው ፊት ያሉ አሽከሮችንም አስወጣቸው፤ ብዙ ጠጥተው ሁሉም ተዳከመው ነበርና ወደ ማደሪያቸው ገቡ። 2ነገር ግን ዮዲት ብቻዋን ከሆሎፎርኒስ ጋር በድንኳኑ ቀረች፥ እርሱ በወይን በጣም ሰክሮ በአልጋው ላይ ተኝቶ ነበር። 3ዮዲት አገልጋይዋን ሌላ ጊዜ እንደምታደርገው እስክትወጣ ድረስ ከመኝታ ቤቱ ውጭ ቆማ እንድትጠብቃት ነገረቻት፤ ለጸሎቷ እንደምትወጣ ነግራታለችና፤ ለባጎስም ይህንኑ ነገረችው። 4ሁሉም ከፊትዋ ወጡ፥ ከትንሽ እስከ ትልቅ ማንም በመኝታ ቤቱ የቀረ አልነበረም። ዮዲት በአልጋው አጠገብ ቆመች፥ በልቧም እንዲህ አለች፦ “የኃይል ሁሉ አምላክ ጌታ ሆይ ስለ ኢየሩሳሌም ክብር በዚች ሰዓት በእጄ የማደርገውን ስራ ተመልከት። 5ርስትህን ለመርዳትና በእኛ ላይ የተነሱብንን ጠላቶቻትንን ለማጥፋት ጊዜው አሁን ነው።” 6በሆሎፎርኒስ ራስ አጠገብ ወዳለው ራስጌ ሄደች፥ ከዛው ሰይፉን መዘዘች። 7ወደ አልጋው ተጠጋች፥ የራሱንም ጠጉር ይዛ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፥ ዛሬ አበርታኝ” አለች። 8በኃይሏ ሁለት ጊዜ አንገቱን መታችው፥ አንገቱን ቆረጠችው። 9ሬሳውን ከአልጋው አንከባለለችው፥ መጋረጃውን ከምሰሶው አወረደች፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወጥታ ለአገልጋይዋ የሆሎፎርኒስን ራስ ሰጠቻት፥ 10እህል በምትይዝበት ከረጢቷ ከተተችው፤ እንደተለመደው ለጸሎት እንደሚሄዱ ሁለቱም አብረው ወጡ፤ ሰፈሩን አቋርጠው ሸለቆውን ዞረው ወደ ቤቱሊያ ተራራ ወጡ፤ ወደ በሮቿም ደረሱ፤
ዮዲት የሆሎፎርኒስን ጭንቅላት ይዛ ወደ ቤጤልዋ ሄደች
11ዮዲትም በሩቅ ሆና በር የሚጠብቁትን ዘበኞች፦ “ክፈቱ፥ በሩን ክፈቱ፥ ዛሬ እንዳደረገው ሁሉ ኃይሉን በእስራኤል ላይ ብርታቱንም በጠላቶቻችን ላይ ያሳይ ዘንድ አምላካችን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” አለቻቸው። 12የከተማይቱ ሰዎች ድምጿን በሰሙ ጊዜ ወደ ከተማቸው በር ፈጥነው ወረዱ፥ የከተማይቱን ሽማግሌዎች ጠሩ። 13መመለሷ የማይታሰብ ነበርና ከትልቁ እስከ ትንሹ ሁሉም እየሮጡ መጡ። በሩንም ከፍተው ተቀበሏቸው፤ ብርሃን እንዲሆን እሳት አንድደው ዙሪያቸውን ከበቡአቸው። 14እርሷም በታላቅ ድምፅ “እግዚአብሔርን አመስግኑት፥ አመስግኑት፥ ምሕረቱን ከእስራኤል ቤት ያላረቀ፥ ነገር ግን ዛሬ በዚህች ሌሊት ጠላቶቻችንን በእኔ እጅ ያጠፋ እግዚአብሔርን አመስግኑ” አለቻቸው። 15ራሱንም ከከረጢቱ አውጥታ አሳየቻቸው፤ እንዲህም አለች፦ “የአሦር ሠራዊት ዋና የጦር አዛዥ የሆሎፎርኒስ ራስ ይኸውላሁ፤ ሰክሮ በተኛበት ቦታ የተጋረደው መጋረጃም ይኸውላችሁ፤ ጌታ በሴት እጅ መታው። 16በሄድሁበት መንገድ በጠበቀኝ በሕያው ጌታ እምላለሁ፥ ለገዛ ጥፋቱ ያማለለው ውበቴ ነበር፤ እኔን የሚሳድፍና የሚያሳፍር ኃጢአት ግን ከእኔ ጋር አልሠራም።” 17ሕዝቡ ሁሉ እጅግ ተደነቁ፤ ሁሉም ሰግደው እግዚአብሔርን አመለኩ፥ በአንድ ድምጽም እንዲህ አሉ፦ “ዛሬ በዚህች ቀን የሕዝብህን ጠላቶች ያዋረድህ አምላካችን ቡሩክ ነህ።” 18#መሳ. 5፥24፤ ሉቃ. 1፥28፤42።ዑዚያም እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በምድር ካሉ ሴቶች ሁሉ ይልቅ በልዑል እግዚአብሔር የተባረክሽ ነሽ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የጠላቶቻችን አለቃ አንገት ለመቁረጥ የመራሽ ጌታ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን። 19ተስፋሽ የእግዚአብሔርን ኃይል ከሚያስታውስ ሰው ልብ ምንጊዜም አይጥፋም። 20አንቺ ሕዝባችን በመዋረዱ ምክንያት ለነፍስሽ ያልሳሳሽ፥ በአምላካችን ፊትም በቀጥታ መንገድ በመሄድ ጥፋታችንን የተከላከልሽ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እንድትከብሪ ያድርግሽ፤ በመልካም ሥራዎችም ይጐብኝሽ።” ሕዝቡም ሁሉ፦ “ይሁን፥ ይሁን” አሉ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ