መጽሐፈ ዮዲት 12
12
1የራሱ የብር ሳህን ወደሚቀመጥበት ድንኳን እንዲያስገቧት አዘዘ፥ እሱ ከሚመገበው ምግብና እሱ ከሚጠጣው ወይን ጠጅ እንዲሰጧት አዘዛቸው። 2ዮዲት ግን “እንቅፋት እንዳይሆንብኝ ከእርሱ አልመገብም ነገር ግን ካመጣሁት እህል እመገባለሁ” አለች። 3ሆሎፎርኒስም “ያመጣሽው ቢያልቅብሽ እንደ እርሱ ያለ ከየት እናመጣልሻለን? ከወገንሽ የሆነ አንድም ከእኛ ጋር የለም” አላት። 4ዮዲትም “ጌታዬ ሕያው ነፍስህን፤ ጌታ ያቀደውን ነገር በእኔ እጅ ስይፈጽም ይዤው የመጣሁትን ባርያህ አልጨርሰውም” አለችው። 5የሆሎፎርኒስ አገልጋዮች ወደ ድንኳኑ አስገቧት፥ እስከ እኩለ ሌሊትም ተኛች። በማለዳ ገና ሳይነጋ ተነሣች፤ 6“እኔ ባርያህ ለጸሎት እንድወጣ እንዲፈቅዱልኝ ጌታዬ ይዘዝ” ብላ ወደ ሆሎፎርኒስ ላከች። 7ሆሎፎርኒስም እንዳይከለክሏት ዘበኞቹን አዘዛቸው። በሰፈሩ ሦስት ቀን ቆየች፤ በየሌሊቱም ወደ ቤቱሊያ ሸለቆ እየሄደች በሰፈሩ በሚገኘው የምንጭ ውኃ ትታጠብ ነበር። 8ከወጣችም በኋላ ስለ ሕየዝቡ መዳን መንገድዋን እንዲያቀናላት ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ ትጸልይ ነበር። 9ንጹህ ሆና ትመለስ ነበር፥ የማታ ምግብዋ እስኪቀርብላት ድረስ በድንኳንዋ ውስጥ ትቆይ ነበር።
ዮዲት በሆሎፎርኒስ ግብዣ ላይ
10በአራተኛው ቀን ሆሎፎርኒስ ለአሽከሮቹ ብቻ ግብዣ አደረገ፤ ከጦር አለቆቹ ማንንም አልጠራም። 11የግሉ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነውን ጃንደረባ ባጎስን እንዲህ አለው፦ “ሂድና በአንተ ጥበቃ ሥር ያለችውን ዕብራዊት ሴት ወደ እኛ መጥታ ከእኛ ጋር እንድትበላና እንድትጠጣ አባብልልኝ፤ 12እንዲህ ያለችውን ሴት ባናነጋግራትና ብንተዋት ለእኛ ውርደት ነው፤ ባንገናኛትም ትስቅብናለች።” 13ባጎስም ከሆሎፎርኒስ ፊት ወጥቶ ወደ እርሷ ገባ፤ እንዲህም አላት፦ “ወደ ጌታዬ ለመምጣት፥ በፊቱም ለመከበር፥ ከእኛ ጋር ወይን ለመጠጣት፥ ዛሬ በናቡከደነፆር ቤት ከሚያገለግሉ የአሦር ልጆች አንዲቱ ለመሆን ይህች ቆንጆ አታመንታ።” 14ዮዲትም “ጌታዬን እምቢ እለው ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ለዓይኑ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ ፈጥኜ አደርጋለሁ፤ እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ ይህ ለእኔ ደስታ ነው።” አለችው። 15ልብስዋን ለመልበስና የሴቶች ጌጣጌጧን ሁሉ ለማድረግ ተነሣች፤ አገልጋይቷም ቀድማ ገባችና በየቀኑ ስትበላ አንጥፋ የምትቀመጥበትን ባጎስ የሰጣትን ምንጣፏን በሆሎፎርኒስ ፊት በምድር ላይ አነጠፈችላት። 16ዮዲትም ገብታ ተቀመጠች፤ የሆሎፎርኒስ ልብ ተደነቀች፤ ከእርሷም ጋር ለመተኛት ነፍሱ ፈጽማ ታወከች፤ እርሷን ካየበት ቀን ጀምሮ እርሷን ለማሳሳት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር፤ 17ሆሎፎርኒስም፦ “ጠጪ፥ ከእኛም ጋር ተደሰቺ” አላት። 18ዮዲትም፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሕይወቴ እንዲህ ከብራ አታውቅምና እጠጣለሁ ጌታዬ” አለችው። 19አገልጋይዋ ያዘጋጀችላትን ተቀብላ በፊቱ በላች፥ ጠጣችም። 20ሆሎፎርኒስ በእርሷ ምክንያት ደስ ብሎት ነበርና ከተወለደበት ጀምሮ አንዲት ቀን እንኳ እንደዚህ ያልጠጣውን ብዙ ወይን ጠጅ ጠጣ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዮዲት 12: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ