መጽሐፈ ዮዲት 14
14
ድል
አይሁዶች የአሦራውያንን ሰፈር አጠቁ
1ዮዲትም እንዲህ አለቻቸው፦ “ወንድሞቼ ስሙኝ፥ ይህን ራስ ውሰዱና በግንቡ ላይ ስቀሉት። 2ጧት ሲነጋና በምድር ላር ፀሐይ ስትወጣ ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ያዙ፤ ለጦር የደረሱ ወንዶች ሁሉ ከከተማይቱ ይውጡ፤ አንድ አለቃ ሹሙ፥ ወደ አሦራውያን ሜዳው የጥበቃ ኬላ የምትወርዱ ምሰሉ፤ ነገር ግን አትውረዱ። 3የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ጦር ሰፈራቸው ይሄዳሉ፤ የአሦርን የጦር ሠራዊት አዛዦችን ይቀሰቅሳሉ፤ ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳን ይሮጣሉ፥ ነገር ግን አያገኙትም። በዚያን ጊዜ ፍርሃት ይይዛቸዋል፥ ከፊታችሁም ይሸሻሉ። 4እናንተና በእስራኤል ዙሪያ የሚኖሩ ሁሉ ተከተሏቸው፥ በመንገዳቸውም ላይ ምቱአቸው። 5ይህን ከማድረጋችሁ በፊት ግን የእስራኤልን ቤት የናቀውንና ከእኛም ጋር እንዲሞት ወደ እኛ የላከውን ሰው እንዲያይና እንዲለይና አሞናዊውን አኪዮርን ጥሩልኝ።” 6አኪዮርን ከዑዚያ ቤት ጠሩት፤ መጥቶም በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ከነበሩት ውስጥ አንድ ሰው የሆሎፎርኒስን ራስ በእጁ ይዞ ባየ ጊዜ በግንባሩ ተደፋ፥ መንፈሱም ከዳው። 7በአነሡትም ጊዜ በዮዲት እግር ሥር ወደቀ፤ ሰገደላትም፥ እንዲህም አለ “በይሁዳ ድንኳኖች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ፤ ስምሽን የሚሰሙ አሕዛብ ሁሉ ይሸበራሉ። 8አሁንም በእነዚህ ቀኖች ያደረግሽውን ሁሉ እስቲ ንገሪኝ።” ዮዲትም ከወጣችበት ቀን ጀምሮ አሁን ንግግር እስከምታደርግበት ጊዜ ድረስ ያደረገችውን ሁሉ በሕዝቡ መካከል አወራችለት። 9ንግግርዋን በጨረሰች ጊዜ ሕዝቡ በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ በከተማቸውም የደስታ ጩኸት ጮኹ። 10አኪዮርም የእስራኤል አምላክ ያደረገውን ሁሉ በአየ ጊዜ ፈጽሞ በእግዚአብሔር አመነ። ሸለፈቱን ተገርዞ የእስራኤልን ቤት ተቀላቀለ፥ እስከ ዛሬ ድረስም አለ። 11በነጋም ጊዜ የሆሎፎርኒስን ራስ በግንቡ ላይ ሰቀሉት፤ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣርያውን ይዞ ሁሉም በጭፍራቸው ሆነው ወደ ተራራው መውረጃ ወጡ። 12የአሦር ልጆችም በአዩአቸው ጊዜ ወደ አለቆቻቸው፥ አለቆቻቸውም ወደ ጦር መሪዎቻቸው፥ ወደ አዛዦቻቸውና ገዢዎቻቸው ሰው ላኩ። 13ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳን መጥተው የግሉ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነውን “ጌታችንን ቀስቅስልን፥ ባሮቹ እስከ መጨረሻው ሊጠፉ ፈልገው ከእኛ ጋር ሊዋጉ ወደዚህ መውረድን ደፍረዋል” አሉት። 14ባጎስም የድንኳኑን በር አንኳኳ፥ ከዮዲት ጋር የተኛ መስሎት ነበርና። 15ነገር ግን የሚሰማው ሲያጣ፥ ገልጦ ወደ መኝታ ቤቱ ገባ፤ ሬሳው መሬት ላይ ወድቆ፥ አንገቱም ተቆርጦ ተወስዶ አገኘው። 16በታላቅ ድምፅ በጣም ጮኸ፥ አለቀሰ፥ አቃሰተ፥ ጮኸ፥ ልብሱንም ቀደደ። 17ዮዲት ወደነበረችበት ድንኳን ገባ፥ አላገኛትምም፥ ወደ ሕዝቡ እየተጣደፈ ወጣና እንዲህ ሲል ጮኸ፦ 18“ባሮቹ አታልለውናል፤ አንዲት ዕብራዊት ሴት የንጉሥ ናቡከደነፆርን ቤት ኀፍረት አከናንባዋለች፤ የሆሎፎርኒስ ሬሣ መሬት ላይ ወድቋል፥ ራሱም በላዩ የለም።” 19የአሦር ጦር ሠራዊት አለቆች ይህንን ቃል በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ነፍሳቸውም በጣም ታወከች፥ ታላቁ ጩኸታቸውና ለቅሶአቸው በጦር ሰፈሩ አስተጋባ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዮዲት 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ