መጽሐፈ መዝሙር 74:12-23

መጽሐፈ መዝሙር 74:12-23 አማ05

አምላክ ሆይ! ከጥንት ጀምሮ ንጉሣችን አንተ ነህ፤ በምድርም ላይ ደኅንነትን አመጣህ፤ በታላቁ ኀይልህ ባሕሩን ከፈልክ፤ በባሕር የሚኖሩትን የታላላቅ አውሬዎች ራስ ቀጠቀጥክ፤ ሌዋታን የተባለውን የባሕር ዘንዶ ራስ ቀጠቀጥህ፤ ሥጋውንም በበረሓ ለሚኖሩ ፍጥረቶች ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው። ምንጮችና ጅረቶች እንዲፈስሱ አደረግህ፤ ታላላቅ ወንዞችን ግን አደረቅህ። ቀኑንና ሌሊቱን የፈጠርክ፥ ፀሐይንና ጨረቃን በየቦታቸው ያጸናህ አንተ ነህ፤ አንተ ለምድር ዳርቻን ወሰንህ፤ ክረምትና በጋ እንዲፈራረቁ አደረግህ። እግዚአብሔር ሆይ፥ ጠላቶችህ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት፤ እነርሱ ሞኞች ስለ ሆኑ ስምህን ይዳፈራሉ። አንተን የሚያምኑትን ነፍሶች ለአራዊት አሳልፈህ አትስጥ፤ የአገልጋዮችህንም ሥቃይ ለዘለዓለም አትርሳ! ከእኛ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስብ፤ ጨለማ በሆነው ምድር ማእዘን ሁሉ ዐመፅ አለ። ጭቈና የደረሰባቸው ሰዎች ዐፍረው ወደ ኋላ እንዲመለሱ አታድርግ፤ ድኾችና ምስኪኖች ስምህን እንዲያመሰግኑ ይሁን። አምላክ ሆይ! ተነሥ! ስምህን የሚዳፈሩትን ተከላከል! እነዚህ ሞኞች ቀኑን ሙሉ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት። ጠላቶችህ ዘወትር የሚጮኹትን ጩኸትና የሚደነፉትን ድንፋታ አስታውስ።