መዝሙር 74:12-23
መዝሙር 74:12-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ አንተ ከጥንት ጀምሮ ንጉሤ ነህ፤ በምድር ላይ ማዳንን አደረግህ። ባሕርን በኀይልህ የከፈልህ አንተ ነህ፤ የባሕሩንም አውሬ ራሶች በውሃ ውስጥ ቀጠቀጥህ። የሌዋታንን ራሶች አደቀቅህ፤ ለምድረ በዳ ፍጥረታትም ምግብ አድርገህ የሰጠሃቸው፣ ምንጮችንና ፈሳሾችን ያፈለቅህ አንተ ነህ፤ ሳያቋርጡ የሚፈስሱትንም ወንዞች አደረቅህ። ቀኑ የአንተ ነው፤ ሌሊቱም የአንተ ነው፤ ጨረቃንና ፀሓይን አንተ አጸናሃቸው። የምድርን ዳርቻ ሁሉ የወሰንህ አንተ ነህ፤ በጋውንም ክረምቱንም አንተ ሠራህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላት እንዴት እንደሚያሾፍ፣ ሞኝ ሕዝብም ስምህን እንዴት እንዳቃለለ ዐስብ። የርግብህን ነፍስ አሳልፈህ ለዱር አራዊት አትስጥ፤ የችግረኞች ሕዝብህን ሕይወት ለዘላለሙ አትርሳ። ኪዳንህን ዐስብ፤ የዐመፅ መናኸሪያ በምድሪቱ ጨለማ ስፍራዎች ሞልተዋልና። የተጨቈኑት ዐፍረው አይመለሱ፤ ድኾችና ችግረኞች ስምህን ያመስግኑ። አምላክ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለዐላማህ ተሟገት፤ ሞኝ ሰው ቀኑን ሙሉ እንደሚያላግጥብህ ዐስብ። የባላጋራዎችህን ድንፋታ፣ ዘወትር የሚነሣውን የጠላቶችህን ፉከራ አትርሳ።
መዝሙር 74:12-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ከጥንት ጀምሮ ንጉሣችን አንተ ነህ፤ በምድርም ላይ ደኅንነትን አመጣህ፤ በታላቁ ኀይልህ ባሕሩን ከፈልክ፤ በባሕር የሚኖሩትን የታላላቅ አውሬዎች ራስ ቀጠቀጥክ፤ ሌዋታን የተባለውን የባሕር ዘንዶ ራስ ቀጠቀጥህ፤ ሥጋውንም በበረሓ ለሚኖሩ ፍጥረቶች ምግብ አድርገህ ሰጠሃቸው። ምንጮችና ጅረቶች እንዲፈስሱ አደረግህ፤ ታላላቅ ወንዞችን ግን አደረቅህ። ቀኑንና ሌሊቱን የፈጠርክ፥ ፀሐይንና ጨረቃን በየቦታቸው ያጸናህ አንተ ነህ፤ አንተ ለምድር ዳርቻን ወሰንህ፤ ክረምትና በጋ እንዲፈራረቁ አደረግህ። እግዚአብሔር ሆይ፥ ጠላቶችህ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት፤ እነርሱ ሞኞች ስለ ሆኑ ስምህን ይዳፈራሉ። አንተን የሚያምኑትን ነፍሶች ለአራዊት አሳልፈህ አትስጥ፤ የአገልጋዮችህንም ሥቃይ ለዘለዓለም አትርሳ! ከእኛ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስብ፤ ጨለማ በሆነው ምድር ማእዘን ሁሉ ዐመፅ አለ። ጭቈና የደረሰባቸው ሰዎች ዐፍረው ወደ ኋላ እንዲመለሱ አታድርግ፤ ድኾችና ምስኪኖች ስምህን እንዲያመሰግኑ ይሁን። አምላክ ሆይ! ተነሥ! ስምህን የሚዳፈሩትን ተከላከል! እነዚህ ሞኞች ቀኑን ሙሉ በአንተ ላይ እንደሚሳለቁ ተመልከት። ጠላቶችህ ዘወትር የሚጮኹትን ጩኸትና የሚደነፉትን ድንፋታ አስታውስ።
መዝሙር 74:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። አንተ ባሕርን በኃይልህ ከፈልካት፥ የአውሬዎችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። አንተ የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፥ ለኢትዮጵያ ሰዎችም እንደ ምግብ ሰጠሃቸው። አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፥ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ። ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፥ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ። አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ አረጋገጥህ፥ በጋንም ክረምትንም አንተ ሠራህ። ይህንንም አስታውስ፥ ጠላት በጌታ ተሳለቀ፥ አላዋቂ ሕዝብም በስምህ ቀለደ። የምትገዛልህን እርግብ ለአራዊት አትስጣት፥ የችግረኞችህን ነፍስ መቼውንም አትርሳ። ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በዓመፅ ቤቶች ተሞልተዋልና። ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፥ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ። አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፥ አላዋቂዎች ዘወትር የተሳለቁብህን አስብ። የጠላቶችህን ቃል አትርሳ፥ የተቃዋሚዎችህ ድንፋታ ሳያቋርጥ ወደ አንተ ይወጣል።