መዝሙር 74:12-23

መዝሙር 74:12-23 NASV

አምላክ ሆይ፤ አንተ ከጥንት ጀምሮ ንጉሤ ነህ፤ በምድር ላይ ማዳንን አደረግህ። ባሕርን በኀይልህ የከፈልህ አንተ ነህ፤ የባሕሩንም አውሬ ራሶች በውሃ ውስጥ ቀጠቀጥህ። የሌዋታንን ራሶች አደቀቅህ፤ ለምድረ በዳ ፍጥረታትም ምግብ አድርገህ የሰጠሃቸው፣ ምንጮችንና ፈሳሾችን ያፈለቅህ አንተ ነህ፤ ሳያቋርጡ የሚፈስሱትንም ወንዞች አደረቅህ። ቀኑ የአንተ ነው፤ ሌሊቱም የአንተ ነው፤ ጨረቃንና ፀሓይን አንተ አጸናሃቸው። የምድርን ዳርቻ ሁሉ የወሰንህ አንተ ነህ፤ በጋውንም ክረምቱንም አንተ ሠራህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላት እንዴት እንደሚያሾፍ፣ ሞኝ ሕዝብም ስምህን እንዴት እንዳቃለለ ዐስብ። የርግብህን ነፍስ አሳልፈህ ለዱር አራዊት አትስጥ፤ የችግረኞች ሕዝብህን ሕይወት ለዘላለሙ አትርሳ። ኪዳንህን ዐስብ፤ የዐመፅ መናኸሪያ በምድሪቱ ጨለማ ስፍራዎች ሞልተዋልና። የተጨቈኑት ዐፍረው አይመለሱ፤ ድኾችና ችግረኞች ስምህን ያመስግኑ። አምላክ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለዐላማህ ተሟገት፤ ሞኝ ሰው ቀኑን ሙሉ እንደሚያላግጥብህ ዐስብ። የባላጋራዎችህን ድንፋታ፣ ዘወትር የሚነሣውን የጠላቶችህን ፉከራ አትርሳ።