እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን እስራኤልን ገና በሕፃንነቱ ወደድኩት፤ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት። ነገር ግን ሕዝቤን እስራኤልን ይበልጥ ወደ እኔ እንዲቀርቡ በጠራኋቸው መጠን፥ እነርሱ ይበልጥ ከእኔ እየራቁ ሄዱ። በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት ከማቅረብና ለምስሎቹም ዕጣን ከማጠን አልተቈጠቡም። እጆቻቸውን ይዤ በእግራቸው መረማመድን ያስተማርኳቸው እኔ ነበርኩ፤ ዕቅፍ አድርጌም ይዤአቸው ነበርኩ፤ እነርሱ ግን እኔ እንደምንከባከባቸው አላወቁም። በሰብአዊ ርኅራኄና በፍቅር ትስስር መራኋቸው፤ ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ በማንሣት እኔ ራሴ ጐንበስ ብዬ መገብኳቸው። “እነርሱ ግን ወደ እኔ መመለስን እምቢ ስላሉ ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤ ለአሦርም ንጉሥ ተገዥዎች ይሆናሉ። የጠላት ጦር ከተሞቻቸውን ይመታል፤ የከተሞቻቸውንም በሮች ይሰባብራል፤ ክፉ ምክራቸውንም ያከሽፋል። ሕዝቤ ከእኔ መራቅን ፈለጉ፤ ይሁን እንጂ ለእርዳታ ወደ ላይ ይጮኻሉ፤ ግን ማንም ከችግራቸው አያወጣቸውም። “እስራኤል ሆይ! እንዴት እተውሃለሁ? እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? በአዳማና በጸቦይም ያደረግኹትንስ፥ እንዴት አደርግብሃለሁ? ለአንተ ያለኝ ፍቅር ታላቅ ስለ ሆነ፥ ይህን ሁሉ ላደርግብህ አልፈቅድም! እኔ በመካከላችሁ የምገኝ ቅዱሱ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁም። ስለዚህ የቊጣዬን መቅሠፍት አላመጣም፤ ዳግመኛም እስራኤልን አላጠፋም፤ በቊጣዬም ወደ እናንተ አልመጣም። “እኔ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን እንደሚያገሣ አንበሳ ድምፄን ሳሰማ እነርሱ ይከተሉኛል፤ ልጆቼም እየተንቀጠቀጡ ከወደ ምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍ ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር እየበረሩ ይመጣሉ፤ ወደ መኖሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ይህን የምናገር እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።”
ትንቢተ ሆሴዕ 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሆሴዕ 11:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች