ሆሴዕ 11:1-11
ሆሴዕ 11:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት፤ አብዝች ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፤ ለበዓሊምም ይሠዉ ነበር፤ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። እኔም ኤፍሬምን ወደድሁት፤ በክንዴም ተቀበልሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ፊቱን በጥፊ እንደሚመቱት ሰው ሆንሁላቸው፤ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እችለውማለሁ። ኤፍሬም በግብፅ ተቀመጠ፤ አሦርም ንጉሡ ነው፤ መመለስን እንቢ ብሎአልና። ጦር በከተማው ደከመች፤ ከእጁም ይለያታል፤ ከሥራቸውም ፍሬ ይበላሉ። ሕዝቤም ከመኖሪያው ተነሥቶአል፤ እግዚአብሔርም በክብሩ ላይ ተቈጣ፤ ከፍ ከፍም አያደርገውም። እኔም “አምልኮቴን ትተሃል አልሁ፤ ኤፍሬም ሆይ! እንዴት አደርግሃለሁ? እስራኤል ሆይ! እንዴትስ እደግፍሃለሁ? እንዴትስ አደርግሃለሁ? እንደ አዳማ ነውን? ወይስ እንደ ሲባዮ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፤ ምሕረቴም ተገልጣለች። እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካካልህም ቅዱሱ ነኝና እንግዲህ የቍጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፤ ኤፍሬምንም ያጠፉት ዘንድ አልተውም፤ ወደ ከተማም አልገባም አልሁ። ጌታ እግዚአብሔርን እከተለው ዘንድ እሄዳለሁ፤ እርሱ ያድነናልና፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ የውኃ ልጆችም ይደነግጣሉ። እንደ ወፍ ከግብፅ፥ እንደ ርግብም ከአሶር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ፤ ወደ ቤታቸውም እመልሳቸዋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር።
ሆሴዕ 11:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እስራኤል ገና ሕፃን ሳለ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። እስራኤል ግን አብዝቼ በጠራኋቸው ቍጥር፣ አብዝተው ከእኔ ራቁ፤ ለበኣል አማልክት ሠዉ፤ ለምስሎችም ዐጠኑ። ኤፍሬምን እጁን ይዤ፣ እንዲራመድ ያስተማርሁት እኔ ነበርሁ፤ ነገር ግን የፈወስኋቸው እኔ እንደ ሆንሁ፣ እነርሱ አላስተዋሉም። በሰው የርኅራኄ ገመድ፣ በፍቅርም ሰንሰለት ሳብኋቸው፤ ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ አነሣሁላቸው፤ ዝቅ ብዬም መገብኋቸው። “ታዲያ ንስሓ መግባትን እንቢ በማለታቸው፣ ወደ ግብጽ አይመለሱምን? አሦርስ አይገዛቸውምን? በከተሞቻቸው ላይ ሰይፍ ይመዘዛል፤ የበሮቻቸውን መወርወሪያ ይቈርጣል፤ ስለ ክፉ ዕቅዳቸውም ይደመስሳቸዋል። ሕዝቤ ከእኔ ዘወር ማለትን መረጡ፤ ወደ ልዑል ቢጣሩም፣ በምንም ዐይነት አያከብራቸውም። “ኤፍሬም ሆይ፤ እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ፤ እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴት እንደ አዳማ አደርግሃለሁ? እንዴትስ እንደ ስቦይ እፈጽምብሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናወጠ፤ ምሕረቴም ሁሉ ተነሣሥቷል። የቍጣዬን መቅሠፍት አላመጣም፤ ተመልሼም ኤፍሬምን አላጠፋም፤ እኔ በመካከላችሁ ያለሁ ቅዱስ አምላክ ነኝ እንጂ፣ ሰው አይደለሁምና፣ በቍጣ አልመጣም። እግዚአብሔርን ይከተላሉ፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ እርሱ ሲያገሣ፣ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍ ከግብጽ፣ እንደ ርግብ ከአሦር፣ እየበረሩ ይመጣሉ፤ እኔም በቤታቸው አኖራቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
ሆሴዕ 11:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፥ ለበኣሊምም ይሠው ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ በእግሩ እንዲሄድ መራሁት፥ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፥ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው። ወደ እኔ ይመለሱ ዘንድ አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል። ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ በከተሞቻቸው ላይ ይወድቃል፥ ከበርቴዎችንም ያጠፋል። ሕዝቤም ከእኔ ይመለሱ ዘንድ ወደዱ፥ ወደ ላይም ቢጠሩአቸው ማንም ከፍ ከፍ ያደርጋቸው ዘንድ አይችልም። ኤፍሬም ሆይ፥ እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ፥ እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አዳማ እጥልሃለሁ? እንዴትስ እንደ ሲባዩ አደርግሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች። እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም አጠፋ ዘንድ አልመለስም፥ በመዓትም አልመጣም። እግዚአብሔርን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፥ ባገሣም ጊዜ ልጆች እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፥ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
ሆሴዕ 11:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን እስራኤልን ገና በሕፃንነቱ ወደድኩት፤ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት። ነገር ግን ሕዝቤን እስራኤልን ይበልጥ ወደ እኔ እንዲቀርቡ በጠራኋቸው መጠን፥ እነርሱ ይበልጥ ከእኔ እየራቁ ሄዱ። በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት ከማቅረብና ለምስሎቹም ዕጣን ከማጠን አልተቈጠቡም። እጆቻቸውን ይዤ በእግራቸው መረማመድን ያስተማርኳቸው እኔ ነበርኩ፤ ዕቅፍ አድርጌም ይዤአቸው ነበርኩ፤ እነርሱ ግን እኔ እንደምንከባከባቸው አላወቁም። በሰብአዊ ርኅራኄና በፍቅር ትስስር መራኋቸው፤ ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ በማንሣት እኔ ራሴ ጐንበስ ብዬ መገብኳቸው። “እነርሱ ግን ወደ እኔ መመለስን እምቢ ስላሉ ወደ ግብጽ ይመለሳሉ፤ ለአሦርም ንጉሥ ተገዥዎች ይሆናሉ። የጠላት ጦር ከተሞቻቸውን ይመታል፤ የከተሞቻቸውንም በሮች ይሰባብራል፤ ክፉ ምክራቸውንም ያከሽፋል። ሕዝቤ ከእኔ መራቅን ፈለጉ፤ ይሁን እንጂ ለእርዳታ ወደ ላይ ይጮኻሉ፤ ግን ማንም ከችግራቸው አያወጣቸውም። “እስራኤል ሆይ! እንዴት እተውሃለሁ? እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? በአዳማና በጸቦይም ያደረግኹትንስ፥ እንዴት አደርግብሃለሁ? ለአንተ ያለኝ ፍቅር ታላቅ ስለ ሆነ፥ ይህን ሁሉ ላደርግብህ አልፈቅድም! እኔ በመካከላችሁ የምገኝ ቅዱሱ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁም። ስለዚህ የቊጣዬን መቅሠፍት አላመጣም፤ ዳግመኛም እስራኤልን አላጠፋም፤ በቊጣዬም ወደ እናንተ አልመጣም። “እኔ እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን እንደሚያገሣ አንበሳ ድምፄን ሳሰማ እነርሱ ይከተሉኛል፤ ልጆቼም እየተንቀጠቀጡ ከወደ ምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍ ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር እየበረሩ ይመጣሉ፤ ወደ መኖሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ይህን የምናገር እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።”
ሆሴዕ 11:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከእኔ ዘንድ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠው ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ መራመድን አስተማርሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። ሰብአዊ በሆነ የርኅራኄ ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ እነርሱንም ጐንበስ ብዬ መገብኳቸው። ወደ እኔ መመለስን አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል። ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ ከተሞቻቸውን ይመታል፥ ምዋርተኞቻቸውንም ይበላል ያጠፋልም። ሕዝቤም ከእኔ ወደ ኋላ መመለስን በጽኑ ወደዱ፤ በአንድነትም ወደ ልዑሉ ይጣራሉ፥ እርሱ ግን ከፍ ከፍ አያደርጋቸውም። ኤፍሬም ሆይ! እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ! እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አድማህ አደርግሃለሁ? እንዴትስ እንደ ጲቦይም እመለከትሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች። እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም ዳግመኛ አላጠፋም፤ በመዓትም አልመጣም። ጌታን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ ባገሣም ጊዜ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ።