ሆሴዕ 11:1-11

ሆሴዕ 11:1-11 NASV

“እስራኤል ገና ሕፃን ሳለ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። እስራኤል ግን አብዝቼ በጠራኋቸው ቍጥር፣ አብዝተው ከእኔ ራቁ፤ ለበኣል አማልክት ሠዉ፤ ለምስሎችም ዐጠኑ። ኤፍሬምን እጁን ይዤ፣ እንዲራመድ ያስተማርሁት እኔ ነበርሁ፤ ነገር ግን የፈወስኋቸው እኔ እንደ ሆንሁ፣ እነርሱ አላስተዋሉም። በሰው የርኅራኄ ገመድ፣ በፍቅርም ሰንሰለት ሳብኋቸው፤ ቀንበሩን ከጫንቃቸው ላይ አነሣሁላቸው፤ ዝቅ ብዬም መገብኋቸው። “ታዲያ ንስሓ መግባትን እንቢ በማለታቸው፣ ወደ ግብጽ አይመለሱምን? አሦርስ አይገዛቸውምን? በከተሞቻቸው ላይ ሰይፍ ይመዘዛል፤ የበሮቻቸውን መወርወሪያ ይቈርጣል፤ ስለ ክፉ ዕቅዳቸውም ይደመስሳቸዋል። ሕዝቤ ከእኔ ዘወር ማለትን መረጡ፤ ወደ ልዑል ቢጣሩም፣ በምንም ዐይነት አያከብራቸውም። “ኤፍሬም ሆይ፤ እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ፤ እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴት እንደ አዳማ አደርግሃለሁ? እንዴትስ እንደ ስቦይ እፈጽምብሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናወጠ፤ ምሕረቴም ሁሉ ተነሣሥቷል። የቍጣዬን መቅሠፍት አላመጣም፤ ተመልሼም ኤፍሬምን አላጠፋም፤ እኔ በመካከላችሁ ያለሁ ቅዱስ አምላክ ነኝ እንጂ፣ ሰው አይደለሁምና፣ በቍጣ አልመጣም። እግዚአብሔርን ይከተላሉ፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ እርሱ ሲያገሣ፣ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። እንደ ወፍ ከግብጽ፣ እንደ ርግብ ከአሦር፣ እየበረሩ ይመጣሉ፤ እኔም በቤታቸው አኖራቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።