ማቴዎስ 2:12-23
ማቴዎስ 2:12-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያን ጊዜ እንዲህ ሲል በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ መጽናናትም አልወደደችም፤ የሉምና።” ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:12-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ጠቢባኑ ከሄዱ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሥ! የምትመለስበትን ጊዜ እስካስታውቅህ ድረስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ በመሸሽ በዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻልና” አለው። ስለዚህም ዮሴፍ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ በዚያም ሄሮድስ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ኖረ። በዚህም፣ “ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት” በማለት ጌታ በነቢዩ አንደበት የተናገረው ቃል ተፈጸመ። ሄሮድስ ጠቢባኑ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ በጣም ተናደደ። ከጠቢባኑ በተነገረው መሠረት፣ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን የቤተ ልሔምንና የአካባቢዋን መንደሮች ወንድ ልጆች ሁሉ ልኮ አስገደለ። በዚህም በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤ መጽናናትም እንቢ አለች፤ ልጆቿ ዐልቀዋልና።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
ማቴዎስ 2:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፦ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፦ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት፦ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:12-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ እግዚአብሔር በሕልም ስላስጠነቀቃቸው፥ ተመራማሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሄዱ። የከዋክብት ተመራማሪዎቹ ከሄዱ በኋላ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፥ “ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ስለሚፈልገው፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ቈይ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍም በሌሊት ተነሣና፥ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ ግብጽ ሄደ። እዚያም ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቈየ፤ ይህም የሆነው ጌታ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ከዚያ በኋላ ሄሮድስ፥ የከዋክብት ተመራማሪዎቹ እንዳታለሉት በተገነዘበ ጊዜ፥ በጣም ተቈጣ፤ ወደ ቤተልሔምና በዙሪያዋም ወዳሉት መንደሮች ሁሉ ወታደሮቹን ልኮ፥ ከከዋክብት ተመራማሪዎቹ በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ዕድሜአቸው ሁለት ዓመት የሆናቸውንና ከዚያ በታች የሆኑትን በቤተልሔምና በአካባቢው የነበሩትን ወንዶች ሕፃናትን አስገደለ። በዚያን ጊዜ፥ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፦ “ራሔል ለልጆችዋ ስታለቅስ፥ የዋይታና፥ የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ልጆችዋም በሕይወት ስለሌሉ ለመጽናናት እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦለት፥ “ሕፃኑን ለመግደል የሚፈልጉት ሰዎች ስለ ሞቱ፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ፥ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። ዮሴፍም ተነሣና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ እስራኤል አገር ተመለሰ። ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ምትክ በይሁዳ ምድር ላይ መንገሡን በሰማ ጊዜ፥ ዮሴፍ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ሆኖም በሕልም መመሪያ ስለ ተሰጠው፥ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ስላስጠነቀቃቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ፥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ፥ ይህም ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ነው። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ወታደሮችን ልኮ ከሰብአ ሰገል በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ የነበሩትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያንጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የብዙ ዋይታ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና መጽናናትን እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው፦ “ተነሣ፤የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ።” እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው እንዲፈጸም፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።