የማቴዎስ ወንጌል 2:12-23
የማቴዎስ ወንጌል 2:12-23 አማ05
ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ እግዚአብሔር በሕልም ስላስጠነቀቃቸው፥ ተመራማሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሄዱ። የከዋክብት ተመራማሪዎቹ ከሄዱ በኋላ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፥ “ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ስለሚፈልገው፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ቈይ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍም በሌሊት ተነሣና፥ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ ግብጽ ሄደ። እዚያም ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቈየ፤ ይህም የሆነው ጌታ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ከዚያ በኋላ ሄሮድስ፥ የከዋክብት ተመራማሪዎቹ እንዳታለሉት በተገነዘበ ጊዜ፥ በጣም ተቈጣ፤ ወደ ቤተልሔምና በዙሪያዋም ወዳሉት መንደሮች ሁሉ ወታደሮቹን ልኮ፥ ከከዋክብት ተመራማሪዎቹ በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ዕድሜአቸው ሁለት ዓመት የሆናቸውንና ከዚያ በታች የሆኑትን በቤተልሔምና በአካባቢው የነበሩትን ወንዶች ሕፃናትን አስገደለ። በዚያን ጊዜ፥ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፦ “ራሔል ለልጆችዋ ስታለቅስ፥ የዋይታና፥ የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ልጆችዋም በሕይወት ስለሌሉ ለመጽናናት እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦለት፥ “ሕፃኑን ለመግደል የሚፈልጉት ሰዎች ስለ ሞቱ፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ፥ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። ዮሴፍም ተነሣና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ እስራኤል አገር ተመለሰ። ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ምትክ በይሁዳ ምድር ላይ መንገሡን በሰማ ጊዜ፥ ዮሴፍ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ሆኖም በሕልም መመሪያ ስለ ተሰጠው፥ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።


