የማቴዎስ ወንጌል 2:12-23
የማቴዎስ ወንጌል 2:12-23 መቅካእኤ
ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ስላስጠነቀቃቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ፥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ፥ ይህም ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ነው። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ወታደሮችን ልኮ ከሰብአ ሰገል በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ የነበሩትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያንጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የብዙ ዋይታ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና መጽናናትን እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው፦ “ተነሣ፤የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ።” እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው እንዲፈጸም፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።


