ኢዮብ 8:1-20
ኢዮብ 8:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አውኬናዊው በልዳዶስ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ “እስከ መቼ ይህን ነገር ትናገራለህ? ወይስ ነገርን የማብዛት መንፈስ በአፍህ አለን? በውኑ እግዚአብሔር በዐመፅ ይፈርዳልን? ሁሉን የፈጠረ አምላክስ ጽድቅን ያጣምማልን? ልጆችህ በፊቱ በድለው እንደ ሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል። “አንተ ግን ወደ እግዚአብሔር ገሥግሥ፥ ሁሉን ወደሚችለው አምላክም ጸልይ፥ ንጹሕና ጻድቅ ብትሆን፥ ልመናህን ፈጥኖ ይሰማሃል፥ የጽድቅህንም ብድራት ፈጽሞ ይሰጥሃል። ጅማሬህም ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ ቍጥር አይኖረውም። ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶችንም በየወገናቸው በትጋት መርምር፥ እኛ የትናንት ብቻ ነን ምንም አናውቅም፤ ሕይወታችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን? “በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን? ገና በሥሩ ሳለ፥ ሳይቈረጥም፥ ውኃ የማይጠጣ ተክል ሁሉ ይደርቃል። እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፤ የዝንጉ ሰውም ተስፋ ትጠፋለች፤ ቤቱም ያለ ነዋሪ ይቀራል፥ ማደሪያውም የሸረሪት ድር ይሆናል። ቤቱን ቢደግፈውም አይቆምለትም፤ የጀመረውንም አይፈጽምም። ከፀሐይ በታች ይሻግታል፤ ጫፉም በአትክልት ቦታ ይወጣል። በድንጋይ ክምር ላይ ያድራል፤ በድንጋዮቹም መካከል ይኖራል። ቦታው ቢውጠው፦ እንደዚህ ያለ አላየሁም ብሎ ይክደዋል። ኀጢአተኞች እንዲሁ ይጠፋሉና፤ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ። እነሆ፥ እግዚአብሔር የዋሁን ሰው አይጥለውም፥ የኀጢኣተኞችንም እጅ አያበረታም። የዝንጉዎችንም መባ አይቀበልም።
ኢዮብ 8:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሹሐዊውም በልዳዶስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንዲህ ያለውን ነገር የምትናገረው፣ ቃልህም እንደ ብርቱ ነፋስ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ፍትሕን ያጣምማልን? ሁሉን ቻይ አምላክስ ጽድቅን ያጣምማልን? ልጆችህ በርሱ ላይ ኀጢአት ሠርተው ከሆነ፣ ለኀጢአታቸው ቅጣት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ነገር ግን አንተ ወደ እግዚአብሔር ብትመለከት፣ ሁሉን ቻይ አምላክን ብትማፀን፣ ንጹሕና ጻድቅ ብትሆን፣ እርሱ ስለ አንተ አሁኑኑ ይነሣል፤ ወደ ተገቢውም ስፍራህ ይመልስሃል። ጅማሬህ አነስተኛ ቢመስልም፣ ፍጻሜህ እጅግ ታላቅ ይሆናል። “የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፤ አባቶቻቸውም የደረሱበትን መርምረህ አግኝ፤ እኛ ትናንት ስለ ተወለድን አንዳች አናውቅምና፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው። እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፣ ከልቦናቸውም ቃልን የሚያወጡ አይደሉምን? ደንገል ረግረግ በሌለበት ስፍራ ይበቅላልን? ቄጠማስ ውሃ በሌለበት ይለመልማልን? ገና በማደግ ላይ እያለ ሳይታጨድ፣ ከሌሎች ሣሮች ፈጥኖ ይደርቃል። እግዚአብሔርን የሚረሱ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤ አምላክ የለሽ ኑሮ የሚኖሩም ሁሉ ተስፋቸው ትጠፋለች። መተማመኛው ቀጭን ክር፣ ድጋፉም የሸረሪት ድር ነው። ድሩ ላይ ቢደገፍ ይበጠስበታል፤ አጥብቆም ቢይዘው አይጸናም። ውሃ እንደ ጠገበ ተክል፣ ፀሓይ እየሞቀው፣ ቅርንጫፉን ሁሉ በአትክልቱ ስፍራ ላይ ይዘረጋል። ሥሩን በድንጋይ ክምር ላይ ይጠመጥማል፤ በዐለትም መካከል ስፍራ ያበጃል። ከስፍራው ሲወገድ ግን፣ ያ ቦታ ‘አይቼህ አላውቅም’ ብሎ ይክደዋል። እነሆ፤ ሕይወቱ በዚህ ያከትማል፤ ሌሎች አትክልትም ከመሬት ይበቅላሉ። “እነሆ፤ እግዚአብሔር እንከን የሌለበትን ሰው አይጥልም፤ የክፉዎችንም እጅ አያበረታም፤
ኢዮብ 8:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ፦ እስከ መቼ ይህን ትናገራለህ? የአፍህስ ቃል እስከ መቼ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል? በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን? ልጆችህ በድለውት እንደ ሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል። እግዚአብሔርን ብትገሠግሥ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትለምን፥ ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት አሁን ስለ አንተ ይነቃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያከናውንልሃል። ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል። ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፥ ምንም አናውቅም፥ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፥ እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን? በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን? ገና ሲለመልም ሳይቈረጥም፥ ከአትክልት ሁሉ በፊት ይደርቃል። እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፥ የዝንጉም ሰው ተስፋ ይጠፋል። ተስፋው ይቈረጣል፥ እምነቱም እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል። ቤቱን ይደግፈዋል፥ አይቆምለትም፥ ይይዘውማል፥ አይጸናለትም። ፀሐይም ሳይተኵስ ይለመልማል፥ ጫፉም በአታክልቱ ቦታ ይወጣል። በድንጋይ ክምር ላይ ሥሩ ይጠመጠማል፥ የድንጋዩቹን ቦታ ይመለከታል። ከቦታው ቢጠፋ፦ አላየሁህም ብሎ ይክደዋል። እነሆ፥ የመንገዱ ደስታ እንዲህ ነው፥ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ። እነሆ፥ እግዚአብሔር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፥ የኃጢአተኞችንም እጅ አያበረታም።
ኢዮብ 8:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሹሐ አገር ሰው የሆነው ቢልዳድ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ ከአንደበትህ የሚወጡት ቃላት እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ እስከ መቼ ድረስ እንደዚህ አድርገህ ትናገራለህ? እግዚአብሔር ፍርድን ከቶ አያጣምምም፤ ሁሉን ቻይ አምላክ ሁልጊዜ ትክክለኛውን ነገር ያደርጋል። ልጆችህ እግዚአብሔርን በድለውት ከሆነ፥ እነርሱ ቅጣታቸውን አግኝተዋል ማለት ነው። ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥ ሁሉን ቻዩን አምላክ ብትለምነው፥ ቀጥተኛና ንጹሕ ከሆንክ፥ እርሱ ፈጥኖ ወደ ተገቢ ቦታህ ይመልስሃል። አጀማመርህ አነስተኛ መስሎ ቢታይም፥ የወደፊት ኑሮህ የተትረፈረፈ ይሆናል። “እስቲ የጥንቱን ትውልድ ጠይቅ የቀድሞ አባቶቻቸውን ልምድ ተመራመር። የእኛ ዕድሜ ገና ትንሽ በመሆኑ ምንም አናውቅም፤ ዕድሜአችንም እንደ ጥላ የሚያልፍ ነው። እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ ካስተዋሉት አፍልቀው አይደለምን? በውኑ ረግረግ ባልሆነ ቦታ ደንገል ይበቅላልን? ውሃስ በሌለበት ቦታ ሸምበቆ ይለመልማልን? ይህ ካልሆነ አድገው ለመቈረጥ ከመብቃታቸው በፊት ከማንኛውም አረንጓዴ ተክል ቀድመው ይደርቃሉ። እግዚአብሔርን የሚረሱ ሰዎች ሁሉ ፍጻሜአቸው ልክ እንደዚሁ ነው፤ እግዚአብሔር የለም የሚሉ ሰዎች ተስፋቸው ይቈረጣል። እንደ ሸረሪት ድር በሚበጠስ ነገር ይታመናሉ፤ ተስፋ የሚያደርጉበት ነገር እንኳ ቢኖር በቀላሉ ይጠፋል። በሸረሪቱ ድር ላይ ቢደገፍ ጸንቶ አይቆምም፤ የሸረሪት ድሩን ቢጨብጥ ይበጠስበታል። “አረም በፀሐይ አቈጥቊጦ በአትክልት ቦታው እንደሚበዛ ክፉ ሰዎችም እንደዚሁ ይበዛሉ። ሥሮቹም በድንጋይ ካብ ላይ ይጠመጠማሉ፤ በየቋጥኙም ላይ ይጣበቃሉ። አንድ ሰው ከቦታው ቢነቅለው የነበረበት ቦታ አይታወቅም። አረሙም በዚህ ዐይነት ይደርቃል፤ ሌሎች አትክልቶችም ከመሬት ያቈጠቊጣሉ። “እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን አይጥላቸውም፤ ክፉዎችንም አይረዳቸውም።
ኢዮብ 8:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሹሐዊውም ቢልዳድ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “እስከ መቼ ይህን ትናገራለህ? የአፍህስ ቃል እስከ መቼ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል? በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን? ልጆችህ በድለውት እንደሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል። እግዚአብሔርን ብትሻ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትማጸን፥ ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት እርሱ አንተን ነቅቶ ይጠብቅሃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያረጋግጥልሃል። ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል።” “እንግዲህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትኩረት ስጥ፥ እኛ የትናንት ብቻ ነን፥ ምንም አናውቅም፤ ቀኖቻችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ናቸውና። እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን?” “በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን? ገና ሲለመልም ሳይቀጠፍም፥ ከአትክልት ሁሉ በፊት ይደርቃል። እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፥ የአምላክ አልባ ሰውም ተስፋ ይጠፋል። ተስፋው ይቈረጣል፥ መተማመኛው እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል። ቤቱን ይደገፈዋል፥ ነገር ግን አይቆምለትም፥ ይይዘውማል፥ አይጸናለትም። ከፀሐይም ትኩሳት በፊት እርጥብ ነው፥ ጫፉም በአታክልቱ ቦታ ይወጣል። በድንጋይ ክምር ላይ ሥሩ ይጠመጠማል፥ የድንጋዩቹን ቦታ ይመለከታል። ከቦታው ቢጠፋ፦ አላየሁህም ብሎ ይክደዋል። እነሆ፥ የመንገዱ ደስታ እንዲህ ነው፥ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ።” “እነሆ፥ እግዚአብሔር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፥ የክፉዎችን እጅ አያበረታም።