አውኬናዊው በልዳዶስ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ “እስከ መቼ ይህን ነገር ትናገራለህ? ወይስ ነገርን የማብዛት መንፈስ በአፍህ አለን? በውኑ እግዚአብሔር በዐመፅ ይፈርዳልን? ሁሉን የፈጠረ አምላክስ ጽድቅን ያጣምማልን? ልጆችህ በፊቱ በድለው እንደ ሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል። “አንተ ግን ወደ እግዚአብሔር ገሥግሥ፥ ሁሉን ወደሚችለው አምላክም ጸልይ፥ ንጹሕና ጻድቅ ብትሆን፥ ልመናህን ፈጥኖ ይሰማሃል፥ የጽድቅህንም ብድራት ፈጽሞ ይሰጥሃል። ጅማሬህም ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ ቍጥር አይኖረውም። ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶችንም በየወገናቸው በትጋት መርምር፥ እኛ የትናንት ብቻ ነን ምንም አናውቅም፤ ሕይወታችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን? “በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን? ገና በሥሩ ሳለ፥ ሳይቈረጥም፥ ውኃ የማይጠጣ ተክል ሁሉ ይደርቃል። እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፤ የዝንጉ ሰውም ተስፋ ትጠፋለች፤ ቤቱም ያለ ነዋሪ ይቀራል፥ ማደሪያውም የሸረሪት ድር ይሆናል። ቤቱን ቢደግፈውም አይቆምለትም፤ የጀመረውንም አይፈጽምም። ከፀሐይ በታች ይሻግታል፤ ጫፉም በአትክልት ቦታ ይወጣል። በድንጋይ ክምር ላይ ያድራል፤ በድንጋዮቹም መካከል ይኖራል። ቦታው ቢውጠው፦ እንደዚህ ያለ አላየሁም ብሎ ይክደዋል። ኀጢአተኞች እንዲሁ ይጠፋሉና፤ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ። እነሆ፥ እግዚአብሔር የዋሁን ሰው አይጥለውም፥ የኀጢኣተኞችንም እጅ አያበረታም። የዝንጉዎችንም መባ አይቀበልም።
መጽሐፈ ኢዮብ 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 8:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች