ዮሐንስ 21:4-14

ዮሐንስ 21:4-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በነጋ ጊዜም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በባ​ሕሩ ዳር ቆሞ ነበር፤ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም አዩት፤ ግን ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ እንደ ሆነ አላ​ወ​ቁም። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ልጆች ሆይ አን​ዳች የሚ​በላ ነገር አላ​ች​ሁን?” አላ​ቸው፤ እነ​ር​ሱም፥ “የለም” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “መረ​ባ​ች​ሁን በታ​ን​ኳ​ዪቱ በስ​ተ​ቀኝ በኩል ጣሉ፤ ታገ​ኛ​ላ​ች​ሁም” አላ​ቸው፤ መረ​ባ​ቸ​ው​ንም በጣሉ ጊዜ ከተ​ያ​ዘው ዓሣ ብዛት የተ​ነሣ ስቦ ማው​ጣት ተሳ​ና​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ይወ​ደው የነ​በረ ያ ደቀ መዝ​ሙ​ርም ለጴ​ጥ​ሮስ፥ “ጌታ​ችን ነው እኮ” አለው፤ ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ጌታ​ችን እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ የሚ​ለ​ብ​ሰ​ውን ልብስ አን​ሥቶ በወ​ገቡ ታጠቀ፤ ራቁ​ቱን ነበ​ርና ወደ ባሕር ተወ​ረ​ወረ። ሌሎች ደቀ መዛ​ሙ​ርት ግን በታ​ንኳ መጡ፤ ከሁ​ለት መቶ ክንድ ያህል በቀር ከም​ድር አል​ራ​ቁም ነበ​ርና፤ ዓሣ የመ​ላ​ባ​ቸ​ውን መረ​ቦ​ቻ​ቸ​ው​ንም እየ​ሳቡ ሄዱ። ወደ ምድ​ርም በወ​ረዱ ጊዜ ፍሙ መርቶ፥ ዓሣም በላዩ ሆኖ፥ እን​ጀ​ራም ተሠ​ርቶ አገኙ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “አሁን ከያ​ዛ​ች​ኋ​ቸው ዓሣ​ዎች አምጡ” አላ​ቸው። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ወደ ታንኳ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላ​ላቅ ዓሣ​ዎ​ችን መልቶ የነ​በ​ረ​ውን መረብ ወደ ምድር ሳበ፤ ብዛ​ቱም ይህን ያህል ሲሆን መረቡ አል​ተ​ቀ​ደ​ደም። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ኑ፥ ምሳ ብሉ” አላ​ቸው፤ ከደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም አንተ ማነህ? ብሎ ሊጠ​ይ​ቀው የደ​ፈረ የለም፤ ጌታ​ችን እንደ ሆነ ዐው​ቀ​ዋ​ልና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መጣና ኅብ​ስ​ቱን አን​ሥቶ ሰጣ​ቸው፤ ከዓ​ሣ​ውም እን​ዲሁ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ከሙ​ታን ተለ​ይቶ ከተ​ነሣ በኋላ ለደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ሲገ​ለ​ጥ​ላ​ቸው ይህ ሦስ​ተኛ ጊዜዉ ነበር።

ዮሐንስ 21:4-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት። እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ እኮ ነው!” የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘልሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስኪ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ ዐምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደ ሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን ሰጣቸው። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

ዮሐንስ 21:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም፦ “ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም፦ “መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ” አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ። ኢየሱስም፦ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም፦ “ኑ፥ ምሳ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ ስንኳ፦ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊመረምረው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።

ዮሐንስ 21:4-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሲነጋ ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች ዓሣ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “መረቡን ከጀልባው በስተቀኝ በኩል ጣሉና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህ መረቡን በባሕሩ ውስጥ ጣሉት፤ ብዙ ዓሣም ከመያዛቸው የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ ነው እኮ!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስ “ጌታ ነው” ማለትን በሰማ ጊዜ ለሥራ ብሎ ልብሱን አውልቆ ስለ ነበረ ወዲያው ልብሱን ለበሰና ወደ ባሕሩ ዘሎ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት መቶ ሜትር ያኽል ብቻ ስለ ነበረ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ከጀልባው በወረዱ ጊዜ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባው ገብቶ መቶ ኀምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣዎች የሞሉበትን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህን ያኽል ብዙ ዓሣ ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “ኑ ብሉ” አላቸው። ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ሁሉም ዐውቀው ስለ ነበር፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። ከዚያም ኢየሱስ መጣና፤ እንጀራውንና ዓሣውን አንሥቶ ሰጣቸው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ወዲህ ደቀ መዛሙርቱ ሲያዩት ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበር።

ዮሐንስ 21:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም “መረቡን በታንኳዪቱ በስተ ቀኝ ጣሉትና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህም ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀመዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ዘለለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ወደ የብስ በወጡ ጊዜ ዓሣ በላዩ የተቀመጠበት ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንንም ያህል ብዙ ዓሣ ይዞ መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳን “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።