የዮሐንስ ወንጌል 21:4-14

የዮሐንስ ወንጌል 21:4-14 አማ05

ሲነጋ ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች ዓሣ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “መረቡን ከጀልባው በስተቀኝ በኩል ጣሉና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህ መረቡን በባሕሩ ውስጥ ጣሉት፤ ብዙ ዓሣም ከመያዛቸው የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ ነው እኮ!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስ “ጌታ ነው” ማለትን በሰማ ጊዜ ለሥራ ብሎ ልብሱን አውልቆ ስለ ነበረ ወዲያው ልብሱን ለበሰና ወደ ባሕሩ ዘሎ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት መቶ ሜትር ያኽል ብቻ ስለ ነበረ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ከጀልባው በወረዱ ጊዜ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባው ገብቶ መቶ ኀምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣዎች የሞሉበትን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህን ያኽል ብዙ ዓሣ ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “ኑ ብሉ” አላቸው። ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ሁሉም ዐውቀው ስለ ነበር፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። ከዚያም ኢየሱስ መጣና፤ እንጀራውንና ዓሣውን አንሥቶ ሰጣቸው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ወዲህ ደቀ መዛሙርቱ ሲያዩት ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበር።