የዮ​ሐ​ንስ ወን​ጌል 21:4-14

የዮ​ሐ​ንስ ወን​ጌል 21:4-14 አማ2000

በነጋ ጊዜም ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በባ​ሕሩ ዳር ቆሞ ነበር፤ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም አዩት፤ ግን ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ እንደ ሆነ አላ​ወ​ቁም። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ልጆች ሆይ አን​ዳች የሚ​በላ ነገር አላ​ች​ሁን?” አላ​ቸው፤ እነ​ር​ሱም፥ “የለም” አሉት። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “መረ​ባ​ች​ሁን በታ​ን​ኳ​ዪቱ በስ​ተ​ቀኝ በኩል ጣሉ፤ ታገ​ኛ​ላ​ች​ሁም” አላ​ቸው፤ መረ​ባ​ቸ​ው​ንም በጣሉ ጊዜ ከተ​ያ​ዘው ዓሣ ብዛት የተ​ነሣ ስቦ ማው​ጣት ተሳ​ና​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ይወ​ደው የነ​በረ ያ ደቀ መዝ​ሙ​ርም ለጴ​ጥ​ሮስ፥ “ጌታ​ችን ነው እኮ” አለው፤ ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ጌታ​ችን እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ የሚ​ለ​ብ​ሰ​ውን ልብስ አን​ሥቶ በወ​ገቡ ታጠቀ፤ ራቁ​ቱን ነበ​ርና ወደ ባሕር ተወ​ረ​ወረ። ሌሎች ደቀ መዛ​ሙ​ርት ግን በታ​ንኳ መጡ፤ ከሁ​ለት መቶ ክንድ ያህል በቀር ከም​ድር አል​ራ​ቁም ነበ​ርና፤ ዓሣ የመ​ላ​ባ​ቸ​ውን መረ​ቦ​ቻ​ቸ​ው​ንም እየ​ሳቡ ሄዱ። ወደ ምድ​ርም በወ​ረዱ ጊዜ ፍሙ መርቶ፥ ዓሣም በላዩ ሆኖ፥ እን​ጀ​ራም ተሠ​ርቶ አገኙ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “አሁን ከያ​ዛ​ች​ኋ​ቸው ዓሣ​ዎች አምጡ” አላ​ቸው። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ወደ ታንኳ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላ​ላቅ ዓሣ​ዎ​ችን መልቶ የነ​በ​ረ​ውን መረብ ወደ ምድር ሳበ፤ ብዛ​ቱም ይህን ያህል ሲሆን መረቡ አል​ተ​ቀ​ደ​ደም። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ኑ፥ ምሳ ብሉ” አላ​ቸው፤ ከደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም አንተ ማነህ? ብሎ ሊጠ​ይ​ቀው የደ​ፈረ የለም፤ ጌታ​ችን እንደ ሆነ ዐው​ቀ​ዋ​ልና። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መጣና ኅብ​ስ​ቱን አን​ሥቶ ሰጣ​ቸው፤ ከዓ​ሣ​ውም እን​ዲሁ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ከሙ​ታን ተለ​ይቶ ከተ​ነሣ በኋላ ለደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ሲገ​ለ​ጥ​ላ​ቸው ይህ ሦስ​ተኛ ጊዜዉ ነበር።