ዮሐንስ 14:22-31
ዮሐንስ 14:22-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የአስቆሮቱ ሰው ያይደለ ይሁዳም፥ “ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ያይደለ ለእኛ ራስህን ትገልጥ ዘንድ እንዳለህ የተናገርኸው ምንድን ነው?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ግን ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህም የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ቃል ነው እንጂ የእኔ ቃል አይደለም። “ከእናንተም ጋር ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ። ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ፤ አትፍሩም። እኔ እንደምሄድ ወደ እናንተም እንደምመለስ የነገርኋችሁን ሰምታችኋል፤ ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ እርሱ አብ ይበልጠኛልና። አሁንም ይህ በሆነ ጊዜ ታምኑ ዘንድ አስቀድሜ ሳይሆን ነገርኋችሁ። እንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፤ የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና፤ በእኔም ላይ ምንም አያገኝም። ነገር ግን አብን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ትእዛዙን እንደ ሰጠኝ እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ተነሡ ከዚህ፤ እንሂድ።
ዮሐንስ 14:22-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም የአስቆሮቱ ያልሆነው ይሁዳ፣ “ጌታ ሆይ፤ ታዲያ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወድደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከርሱም ጋራ እንኖራለን። የማይወድደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “አሁን ከእናንተ ጋራ እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም። “ ‘እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ማለቴን ሰምታችኋል፤ ብትወድዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ የተናገርሁት ሲፈጸም እንድታምኑ፣ ከመሆኑ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ። የዚህ ዓለም ገዥ ስለሚመጣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋራ ብዙ አልናገርም። እርሱም በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድድ፣ አባቴ ያዘዘኝንም እንደማደርግ ዓለም እንዲያውቅ ነው። “ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።
ዮሐንስ 14:22-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ፦ “ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን። ነግሬአችኋለሁ። ከእእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።
ዮሐንስ 14:22-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አስቆሮታዊው ሳይሆን ሌላው ይሁዳ፥ “ጌታ ሆይ! ራስህን ለዓለም ሳይሆን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ እኛ ወደ እርሱ መጥተን ከእርሱ ጋር አብረን እንኖራለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “አሁን ከእናንተም ጋር እያለሁ ይህን ነገር ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በእኔ ስም የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኳችሁንም ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል። “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዐይነት አይደለም፤ ልባችሁ አይጨነቅ፤ ደግሞም አይፍራ። ‘እኔ እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ እንዳልኩ ሰምታችኋል፤ አባቴ ከእኔ ስለሚበልጥ ብትወዱኝስ ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንድታምኑ፥ ከመሆኑ በፊት አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን መምጣቱ ስለ ሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም። እርሱ በእኔ ላይ ምንም ኀይል የለውም፤ ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድ ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ተነሡ ከዚህ እንሂድ።
ዮሐንስ 14:22-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የአስቆሮቱ ሳይሆን ሌላኛው ይሁዳ “ጌታ ሆይ! ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “በእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም። ልባችሁ አይታወክ፤ አይፍራም። እኔ እሄዳለሁ፤ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝ ቢሆን፥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ በተሰኛችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣልና። ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን ነግሬአችኋለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፤ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም ምንም ኃይል የለውም፤ ነገር ግን አብን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ፥ አብ እንዳዘዘኝ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።