የዮሐንስ ወንጌል 14:22-31

የዮሐንስ ወንጌል 14:22-31 መቅካእኤ

የአስቆሮቱ ሳይሆን ሌላኛው ይሁዳ “ጌታ ሆይ! ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “በእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም። ልባችሁ አይታወክ፤ አይፍራም። እኔ እሄዳለሁ፤ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝ ቢሆን፥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ በተሰኛችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣልና። ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን ነግሬአችኋለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፤ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም ምንም ኃይል የለውም፤ ነገር ግን አብን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ፥ አብ እንዳዘዘኝ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።