የዮሐንስ ወንጌል 14:22-31

የዮሐንስ ወንጌል 14:22-31 አማ05

አስቆሮታዊው ሳይሆን ሌላው ይሁዳ፥ “ጌታ ሆይ! ራስህን ለዓለም ሳይሆን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ እኛ ወደ እርሱ መጥተን ከእርሱ ጋር አብረን እንኖራለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “አሁን ከእናንተም ጋር እያለሁ ይህን ነገር ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በእኔ ስም የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኳችሁንም ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል። “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዐይነት አይደለም፤ ልባችሁ አይጨነቅ፤ ደግሞም አይፍራ። ‘እኔ እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ እንዳልኩ ሰምታችኋል፤ አባቴ ከእኔ ስለሚበልጥ ብትወዱኝስ ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንድታምኑ፥ ከመሆኑ በፊት አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን መምጣቱ ስለ ሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም። እርሱ በእኔ ላይ ምንም ኀይል የለውም፤ ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድ ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ተነሡ ከዚህ እንሂድ።