መሳፍንት 5:19-31
መሳፍንት 5:19-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገሥታት መጡ፤ ተዋጉም፤ በዚያ ጊዜ በመጌዶ ውኆች አጠገብ በቶናሕ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ በቅሚያም ብርን አልወሰዱም። ከዋክብት በሰማይ ተዋጉ፤ በሰልፋቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በርቺ። ያን ጊዜ ከኀያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ፥ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። የእግዚአብሔር መልአክ አለ፥ “ሜሮዝን ርገሙ፤ ወደ እግዚአብሔር ርዳታ አልመጡምና፥ በኀያላን መካከል ወደ እርሱ ርዳታ አልመጡምና፥ በቤቶችዋ ያሉትን ሰዎች ፈጽማችሁ ርገሙ።” የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል፥ ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። ውኃ ለመነ፤ ወተትም ሰጠችው፤ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት። ግራ እጅዋን ወደ ካስማ፤ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታችው፤ ራሱንም ቸነከረች፤ ጆሮ ግንዱንም በሳች፤ ጐዳችውም። በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፤ ወደቀ፤ ተኛ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተፈራገጠ፤ በተፈራገጠበትም በዚያ ተጐሳቍሎ ሞተ። የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ በሰቅሰቅም ዘልቃ፦ ከሲሣራ የተመለሰ እንዳለ አየች፤ ስለምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች። ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦ ምርኮውን ሲካፈል፥ በኀያላኑም ቸብቸቦ ላይ ወዳጆችን ሲወዳጅ ያገኙት አይደለምን? የሲሣራ ምርኮ በየኅብሩ ነበረ፤ የኅብሩም ቀለም የተለያየ ነበረ፤ የማረከውም ወርቀ ዘቦ ግምጃ በአንገቱ ላይ ነበረ። አቤቱ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኀይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፤ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።
መሳፍንት 5:19-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ነገሥታት መጡ፤ ተዋጉም፤ የከነዓን ነገሥታት፣ በመጊዶ ውሆች አጠገብ በታዕናክ ተዋጉ፤ ብርም ሆነ ሌላ ምርኮ ተሸክመው አልሄዱም። ከሰማያት ከዋክብት ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ሲሣራን ገጠሙት። ጥንታዊው ወንዝ፣ የቂሶን ወንዝ፣ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው፤ ነፍሴ ሆይ፤ በኀይል ገሥግሺ የፈረሶች ኰቴ ድምፅ በኀይል ተሰማ፤ ጋለቡ፤ በኀይልም ፈጥነው ጋለቡ። የእግዚአብሔር መልአክ፣ ‘ሜሮዝን ርገሙ፤’ ‘ሕዝቧንም ዐብራችሁ ርገሙ፤ ከኀያላን ሰልፍ እግዚአብሔርን ለመርዳት፣ በእግዚአብሔርም ጐን ለመቆም አልመጡምና’ አለ። “የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል፣ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶች ሁሉ የተባረከች ትሁን። ውሃ ለመነ፤ ወተት ሰጠችው፤ ለመኳንንት በሚገባ ዕቃ፣ ርጎ አቀረበችለት። እጇ ካስማ ያዘ፤ ቀኝ እጇም የሠራተኛ መዶሻ ጨበጠ፤ ሲሣራን መታችው፤ ራሱንም ተረከከችው፤ ክፉኛ ወጋችው፤ ጆሮ ግንዱን በሳችው። በእግሯ ሥር ተደፋ፤ ወደቀ፤ በዚያም ተዘረረ፤ በእግሯ ሥር ተደፋ፤ ወደቀ፤ በተደፋበት በዚያ ወደቀ፤ ሞተም። “የሲሣራ እናት በመስኮት ተመለከተች፤ በዐይነ ርግቡ ቀዳዳም ጮኻ ተጣራች፤ ‘ለምን ሠረገላው ሳይመጣ ዘገየ? የሠረገሎቹስ ድምፅ ለምን ጠፋ?’ አለች። ብልኀተኞች ወይዛዝርቷም መለሱላት፤ እርሷ ግን ለራሷ እንዲህ አለች፤ ‘ምርኮ አግኝተው እየተከፋፈሉ፣ እያንዳንዱም ሰው አንዲት ወይም ሁለት ልጃገረዶች እየወሰደ አይደለምን? ይህ ሁሉ ምርኮ፣ በቀለም ያጌጡ ልብሶች ለሲሣራ ደርሰውት፣ በጌጣጌጥ የተጠለፉ ልብሶች ለዐንገቴ ይዞልኝ እየመጣ አይደለምን?’ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፤ አንተን የሚወድዱህ ግን፣ የንጋት ፀሓይ በኀይል እንደሚወጣ እንዲያ ይሁኑ።” ከዚያም በኋላ ምድሪቱ ለአርባ ዓመት ሰላም አገኘች።
መሳፍንት 5:19-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ። ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። የእግዚአብሔር መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥ እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ። የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት። እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም። በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ። ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦ ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች። ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦ ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጉር ልብስ። አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።
መሳፍንት 5:19-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመጊዶ ውሃ አጠገብ በታዕናክ፥ ነገሥታቱ መጥተው ተዋጉ፤ ከዚያም የከነዓንን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ምርኮ አላገኙም። በሰማይ ከዋክብት ተዋጉ፤ በሂደታቸው ሲሣራንም ጦርነት ገጠሙት። የቂሶን ጐርፍ ጠራረጋቸው፤ የጥንቱ የቂሶን ወንዝ በጐርፉ ወሰዳቸው፤ ነፍሴ ሆይ! በርቺ! ገሥግሺ! ፈረሰኞች እየጋለቡ ሲመጡ የፈረሶቹ ኮቴዎች የነጐድጓድ ድምፅ አሰሙ። የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለ፤ “ሜሮዝን ርገሙ! እዚያ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽማችሁ ርገሙ! እነርሱ በእግዚአብሔር ጐን አልቆሙም፤ ስለ እርሱም ለመዋጋት አልተሰለፉም።” የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል፥ ከሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶችም ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ ሲሣራ “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርስዋ ግን ወተት አቀረበችለት፤ በተከበረ ጽዋ እርጎ አመጣችለት። እንዲሁም በአንድ እጅዋ የድንኳን ካስማ፥ በቀኝ እጅዋ የሠራተኛ መዶሻ ያዘች፤ ሲሣራንም መታ የራስ ቅሉን አደቀቀችው፤ ጆሮ ግንዱንም ቸነከረችው። በእግሮችዋ ሥር ተዝለፍልፎ ወደቀ፤ በእግሮችዋ ሥር ተደፋ፤ በወደቀበትም በዚያው ሞተ። የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ በዐይነ ርግብ ቀዳዳም አተኲራ አየች፤ “የልጄ ሠረገላ ለምን ዘገየ? የሠረገላዎቹ ፈረሶች የኮቴ ድምፅስ ለምን ዘገየ?” ስትል ጠየቀች። ጥበበኞች የሆኑ ወይዛዝሮችዋም መልስ ሰጡአት፤ በእርግጥ እርስዋ ለራስዋ መልስዋን አገኘች። “ምርኮ አግኝተው በመካከላቸው እየተከፋፈሉ አይደለምን? አንድ ወይም ሁለት ቈነጃጅት ለያንዳንዱ ወንድ፥ ለሲሣራ በልዩ ልዩ ቀለማት ያጌጠ የልብስ ምርኮ፥ ለእኔም ለአንገቴ በአንገቴ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጒርጒር ልብስ፥” እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህን ሁሉ በዚህ ዐይነት አጥፋ፤ ወዳጆችህ ግን እንደ ንጋት ፀሐይ ይድመቁ።
መሳፍንት 5:19-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ። ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። የጌታ መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥ ጌታን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ ጌታን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ። የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥ በተከበረ ጽዋ እርጎ አቀረበችለት። እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም። በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ። ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦ “ስለምን ለመምጣት ሠረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሠረገላው መንኰራኵር ቈየ?” ብላ ጮኸች። ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥ እርሷ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦ “ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጉርጉር ልብስ።” አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።