ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ። ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። የእግዚአብሔር መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥ እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ። የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት። እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም። በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ። ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦ ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች። ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦ ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጉር ልብስ። አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።
መጽሐፈ መሳፍንት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 5:19-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች