መጽሐፈ መሳፍንት 5:19-31

መጽሐፈ መሳፍንት 5:19-31 አማ05

በመጊዶ ውሃ አጠገብ በታዕናክ፥ ነገሥታቱ መጥተው ተዋጉ፤ ከዚያም የከነዓንን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ምርኮ አላገኙም። በሰማይ ከዋክብት ተዋጉ፤ በሂደታቸው ሲሣራንም ጦርነት ገጠሙት። የቂሶን ጐርፍ ጠራረጋቸው፤ የጥንቱ የቂሶን ወንዝ በጐርፉ ወሰዳቸው፤ ነፍሴ ሆይ! በርቺ! ገሥግሺ! ፈረሰኞች እየጋለቡ ሲመጡ የፈረሶቹ ኮቴዎች የነጐድጓድ ድምፅ አሰሙ። የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለ፤ “ሜሮዝን ርገሙ! እዚያ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽማችሁ ርገሙ! እነርሱ በእግዚአብሔር ጐን አልቆሙም፤ ስለ እርሱም ለመዋጋት አልተሰለፉም።” የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል፥ ከሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶችም ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ ሲሣራ “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርስዋ ግን ወተት አቀረበችለት፤ በተከበረ ጽዋ እርጎ አመጣችለት። እንዲሁም በአንድ እጅዋ የድንኳን ካስማ፥ በቀኝ እጅዋ የሠራተኛ መዶሻ ያዘች፤ ሲሣራንም መታ የራስ ቅሉን አደቀቀችው፤ ጆሮ ግንዱንም ቸነከረችው። በእግሮችዋ ሥር ተዝለፍልፎ ወደቀ፤ በእግሮችዋ ሥር ተደፋ፤ በወደቀበትም በዚያው ሞተ። የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ በዐይነ ርግብ ቀዳዳም አተኲራ አየች፤ “የልጄ ሠረገላ ለምን ዘገየ? የሠረገላዎቹ ፈረሶች የኮቴ ድምፅስ ለምን ዘገየ?” ስትል ጠየቀች። ጥበበኞች የሆኑ ወይዛዝሮችዋም መልስ ሰጡአት፤ በእርግጥ እርስዋ ለራስዋ መልስዋን አገኘች። “ምርኮ አግኝተው በመካከላቸው እየተከፋፈሉ አይደለምን? አንድ ወይም ሁለት ቈነጃጅት ለያንዳንዱ ወንድ፥ ለሲሣራ በልዩ ልዩ ቀለማት ያጌጠ የልብስ ምርኮ፥ ለእኔም ለአንገቴ በአንገቴ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጒርጒር ልብስ፥” እግዚአብሔር ሆይ! ጠላቶችህን ሁሉ በዚህ ዐይነት አጥፋ፤ ወዳጆችህ ግን እንደ ንጋት ፀሐይ ይድመቁ።