ኢሳይያስ 63:7-16

ኢሳይያስ 63:7-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በስ​ጦ​ታው ሁሉ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቸር​ነ​ትና የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ምስ​ጋና ዐሰ​ብሁ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለእ​ስ​ራ​ኤል ወገ​ኖች እው​ነ​ተኛ ፈራጅ ነው፤ እንደ ቸር​ነ​ቱና እንደ ጽድቁ ብዛ​ትም ይቅ​ር​ታ​ውን ያመ​ጣ​ል​ናል። እር​ሱም፥ “ሕዝቤ ልጆች አይ​ደ​ሉ​ምን? ካል​ከ​ዱ​ኝስ ከመ​ከ​ራ​ቸው ሁሉ አድ​ና​ቸ​ዋ​ለሁ” አለ። በመ​ል​እ​ክ​ተ​ኛም አይ​ደ​ለም፤ በመ​ል​አ​ክም አይ​ደ​ለም፤ እርሱ ራሱ ያድ​ና​ቸ​ዋል እንጂ። እርሱ ይወ​ዳ​ቸ​ዋ​ልና፥ ይራ​ራ​ላ​ቸ​ዋ​ል​ምና እርሱ ተቤ​ዣ​ቸው፤ ተቀ​በ​ላ​ቸ​ውም፤ በዘ​መ​ና​ቸ​ውም ሁሉ ለዘ​ለ​ዓ​ለም አከ​በ​ራ​ቸው። እነ​ርሱ ግን ዐመ​ፁ​በት፤ ቅዱስ መን​ፈ​ሱ​ንም አስ​መ​ረሩ፤ ስለ​ዚህ ተመ​ልሶ ጠላት ሆና​ቸው፤ እር​ሱም ተዋ​ጋ​ቸው። እር​ሱም እን​ዲህ ብሎ የቀ​ደ​መ​ውን ዘመን ዐሰበ፥ “በበ​ጎቹ እረኛ እጅ ከግ​ብፅ በወጡ ጊዜ መል​አ​ኬን በፊ​ታ​ቸው ላክሁ። በሙ​ሴም ቀኝ እጅ ውኃ​ውን ከፈ​ልሁ፤” ውኃ​ውም ተከ​ፍሎ በፊቱ ጸና፤ የዘ​ለ​ዓ​ለም ስም​ንም አደ​ረ​ገ​ለት። ፈረስ በም​ድረ በዳ እን​ደ​ሚ​ያ​ልፍ፥ በቀ​ላይ ውስጥ አሳ​ለ​ፋ​ቸው፥ እነ​ር​ሱም አል​ደ​ከ​ሙም። ወደ ሸለቆ እን​ደ​ሚ​ወ​ርዱ ከብ​ቶች፥ እን​ዲሁ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈስ ወደ ዕረ​ፍት አመ​ጣ​ቸው፤ እን​ዲ​ሁም ለራ​ስህ የከ​በረ ስምን ታደ​ርግ ዘንድ ሕዝ​ብ​ህን መራህ። ከሰ​ማይ ተመ​ለስ፤ ከቅ​ድ​ስ​ና​ህና ከክ​ብ​ርህ ማደ​ሪ​ያም ተመ​ል​ከት፤ ቅን​አ​ት​ህና ኀይ​ል​ህስ ወዴት ነው? የቸ​ር​ነ​ት​ህና የይ​ቅ​ር​ታህ ብዛት ወዴት ነው? ቸል ብለ​ሃ​ልና። አንተ አባ​ታ​ችን ነህ፤ አብ​ር​ሃም ግን አላ​ወ​ቀ​ንም፤ እስ​ራ​ኤ​ልም አል​ተ​ገ​ነ​ዘ​በ​ንም፤ ነገር ግን አንተ አባ​ታ​ችን አድ​ነን፤ ስም​ህም ለዘ​ለ​ዓ​ለም በእኛ ላይ ነው።

ኢሳይያስ 63:7-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ እግዚአብሔር ስላደረገልን ሁሉ፣ ስለሚመሰገንበት ሥራው፣ እንደ ፍቅሩና እንደ ቸርነቱ መጠን፣ ለእስራኤል ቤት ያደረገውን፣ አዎን፣ ስላደረገው መልካም ነገር እናገራለሁ። እርሱም፣ “ርግጥ ነው፤ እነርሱ ሕዝቤ ናቸው፤ የማይዋሹኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው” አለ። ስለዚህም አዳኝ ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ፤ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በምሕረቱ ዋጃቸው፤ በቀደመው ዘመን ሁሉ አነሣቸው፤ ተሸከማቸውም። እነርሱ ግን ዐመፁ፤ ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፤ እርሱ ራሱ ተዋጋቸው። ከዚያም ሕዝቡ የጥንቱን ዘመን፣ የሙሴንና የሕዝቡን ጊዜ እንዲህ በማለት አስታወሱ፤ የበጎቹን እረኛ፣ ከባሕሩ ያወጣቸው እርሱ የት አለ? ቅዱስ መንፈሱንም፣ በመካከላቸው ያኖረ እርሱ የት አለ? የከበረው ኀያል ክንድ፣ በሙሴ ቀኝ እጅ ላይ እንዲያርፍ አደረገ፤ ለራሱ የዘላለም ዝና እንዲሆንለት፣ ውሆችን በፊታቸው ከፈለ። ፈረስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ ሁሉ፣ እነርሱንም በጥልቁ ውስጥ አሳልፎ መራቸው፤ ስለዚህም አልተሰናከሉም፤ ወደ ሸለቆ እንደሚወርድ የከብት መንጋ፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍት ተሰጣቸው። ሕዝብህን በዚህ ሁኔታ የመራሃቸው፣ ስምህን የከበረ ለማድረግ ነው። ከተቀደሰው፣ ከተከበረውና ከፍ ካለው ዙፋንህ፣ ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ ኀይልህና ቅናትህ የት አለ? ገርነትህና ርኅራኄህ ከእኛ ርቀዋል። አብርሃም ባያውቀን፣ እስራኤልም ባያስታውሰን እንኳ፣ አንተ እኮ አባታችን ነህ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ ከጥንትም ቢሆን ስምህ “ቤዛችን” ነው።

ኢሳይያስ 63:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ። እርሱም፦ በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፥ መድኃኒትም ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፥ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፥ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው። እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን አሰበ፦ የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለ? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለ? የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ እንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፥ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፥ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ። አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፥ አቤቱ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።

ኢሳይያስ 63:7-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ለእኛ ስላደረጋቸው ድርጊቶች ሁሉ፥ ለእስራኤል ሕዝብ እንደ መሐሪነቱ ስላሳየው ከፍተኛ በጎ አመለካከት፥ ስለ ተትረፈረፈውም ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የእግዚአብሔርን ቸርነት ምስጉን ድርጊቶቹን እዘረዝራለሁ። እግዚአብሔር “በእርግጥ እነርሱ የእኔ ወገኖችና የማይዋሹ ልጆች ናቸው” አለ። ለእነርሱም አዳኛቸው ሆነ። በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ያዳናቸው በመልእክተኛ ወይም በመልአክ አማካይነት ሳይሆን እርሱ በመካከላቸው በመገኘት ነው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ታደጋቸው፤ እርሱም በቀድሞ ዘመናት ሁሉ አንሥቶ ልጁን እንደሚሸከም ሰው ተንከባከባቸው። ሆኖም እነርሱ የእርሱን ቅዱስ መንፈስ አሳዘኑ፤ ስለዚህ እሱ በእነርሱ ላይ ተነሥቶ ቀጣቸው። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የነበረበትን የቀድሞውን ዘመን ማስታወስ ጀመሩ፤ ከመንጋዎቹ እረኞች ጋር ከባሕር ያወጣቸው እግዚአብሔር የት አለ? ቅዱስ መንፈሱን በውስጣቸው ያሳደረው እግዚአብሔር የት ነው? ለራሱ ዘለዓለማዊ ስም ይሆን ዘንድ በፊታቸው ውሃን ለመክፈል ክብርን የተመላ ኀይሉን በሙሴ ቀኝ በኩል እንዲራመድ ያደረገው የት አለ? በጥልቁ ሲሄዱ እንዳይሰናከሉ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ እንዳለ ፈረስ አደረጋቸው። እንዲሁም በሸለቆው ውስጥ እንደሚሄድ የከብት መንጋ የእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍትን ሰጣቸው። ስምህ ይከብር ዘንድ ሕዝብህን በዚህ ዐይነት መራሃቸው። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ከተቀደሰውና ከክቡር መኖሪያህ ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ ቅንአትህና ኀይልህ የት አሉ? መልካም ፈቃድህና ርኅራኄህስ የት አለ? እነርሱ ከእኛ ርቀዋል። አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤል ባይቀበለንም እንኳ አንተ አባታችን ነህ፤ አምላክ ሆይ! ስምህ ከጥንት እንደ ሆነ ሁሉ አንተ አባታችን ነህ፤ አንተ ታዳጊአችን ነህ።

ኢሳይያስ 63:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታ ስላደረገልን ሁሉ፥ የጌታን ቸርነትና የጌታን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን የተትረፈረፈ ጽኑ ፍቅር እናገራለሁ። እርሱም፦ “በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው” አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ጠላታቸው ሆነ፤ እርሱ ራሱ ተዋጋቸው። እርሱም የቀደመውን ዘመን እንዲህ ብሎ አሰበ፦ የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለው? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለው? የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘለዓለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ እንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የጌታ መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ለእኔ ተከለከለ? አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ ጌታ አንተ አባታችን ነህ፤ ስምህም ከዘለዓለም ታዳጊያችን ነው።