ትንቢተ ኢሳይያስ 63:7-16

ትንቢተ ኢሳይያስ 63:7-16 አማ05

ለእኛ ስላደረጋቸው ድርጊቶች ሁሉ፥ ለእስራኤል ሕዝብ እንደ መሐሪነቱ ስላሳየው ከፍተኛ በጎ አመለካከት፥ ስለ ተትረፈረፈውም ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የእግዚአብሔርን ቸርነት ምስጉን ድርጊቶቹን እዘረዝራለሁ። እግዚአብሔር “በእርግጥ እነርሱ የእኔ ወገኖችና የማይዋሹ ልጆች ናቸው” አለ። ለእነርሱም አዳኛቸው ሆነ። በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ያዳናቸው በመልእክተኛ ወይም በመልአክ አማካይነት ሳይሆን እርሱ በመካከላቸው በመገኘት ነው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ታደጋቸው፤ እርሱም በቀድሞ ዘመናት ሁሉ አንሥቶ ልጁን እንደሚሸከም ሰው ተንከባከባቸው። ሆኖም እነርሱ የእርሱን ቅዱስ መንፈስ አሳዘኑ፤ ስለዚህ እሱ በእነርሱ ላይ ተነሥቶ ቀጣቸው። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የነበረበትን የቀድሞውን ዘመን ማስታወስ ጀመሩ፤ ከመንጋዎቹ እረኞች ጋር ከባሕር ያወጣቸው እግዚአብሔር የት አለ? ቅዱስ መንፈሱን በውስጣቸው ያሳደረው እግዚአብሔር የት ነው? ለራሱ ዘለዓለማዊ ስም ይሆን ዘንድ በፊታቸው ውሃን ለመክፈል ክብርን የተመላ ኀይሉን በሙሴ ቀኝ በኩል እንዲራመድ ያደረገው የት አለ? በጥልቁ ሲሄዱ እንዳይሰናከሉ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ እንዳለ ፈረስ አደረጋቸው። እንዲሁም በሸለቆው ውስጥ እንደሚሄድ የከብት መንጋ የእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍትን ሰጣቸው። ስምህ ይከብር ዘንድ ሕዝብህን በዚህ ዐይነት መራሃቸው። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ከተቀደሰውና ከክቡር መኖሪያህ ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ ቅንአትህና ኀይልህ የት አሉ? መልካም ፈቃድህና ርኅራኄህስ የት አለ? እነርሱ ከእኛ ርቀዋል። አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤል ባይቀበለንም እንኳ አንተ አባታችን ነህ፤ አምላክ ሆይ! ስምህ ከጥንት እንደ ሆነ ሁሉ አንተ አባታችን ነህ፤ አንተ ታዳጊአችን ነህ።