ትንቢተ ኢሳይያስ 63:7-16

ትንቢተ ኢሳይያስ 63:7-16 መቅካእኤ

ጌታ ስላደረገልን ሁሉ፥ የጌታን ቸርነትና የጌታን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን የተትረፈረፈ ጽኑ ፍቅር እናገራለሁ። እርሱም፦ “በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው” አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ጠላታቸው ሆነ፤ እርሱ ራሱ ተዋጋቸው። እርሱም የቀደመውን ዘመን እንዲህ ብሎ አሰበ፦ የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለው? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለው? የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘለዓለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ እንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የጌታ መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ለእኔ ተከለከለ? አብርሃም ባያውቀን፥ እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ ጌታ አንተ አባታችን ነህ፤ ስምህም ከዘለዓለም ታዳጊያችን ነው።