ሕዝቅኤል 41:1-26
ሕዝቅኤል 41:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ መቅደሱም አገባኝ፤ የግንቡንም አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ፥ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። የመግቢያውም ወርድ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የመግቢያውም መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ፥ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱንም አርባ ክንድ፥ ወርዱንም ሃያ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ውስጥም ገባ፤ የመግቢያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፤ የመግቢያውም ግንብ ወርድ በዚህ ወገን ሰባት ክንድ፥ በዚያም ወገን ሰባት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ፊት ርዝመቱን አርባ ክንድ፥ ወርዱንም ሃያ ክንድ አድርጎ ለካና፥ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። የመቅደሱንም ግንብ ስድስት ክንድ፥ በመቅደሱም ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ በሦስት ደርብ ነበሩ፤ በእያንዳንዱም ደርብ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በመቅደሱም ግንብ ዙሪያ ደገፋዎች ይሆኑ ዘንድ አረፍቶች ነበሩ፤ ከመቅደሱ ግንብ ጋር ግንአልተያያዙም ነበር። በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው፥ ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ሦስተኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። ለመቅደሱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ወርድ አምስት ክንድ ነበረ፤ በመቅደሱም ጓዳዎች አጠገብ የቀረ አንድ ባዶ ስፍራ ነበረ። በዕቃ ቤቶቹም መካከል ወርዱ በቤቱ ዙሪያ ሁሉ ሃያ ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም መግቢያ ብቻውን ወደሚኖረው ስፍራ ነበረ፤ አንዱ ደጅ ወደ ሰሜን መንገድ፤ አንዱም ደጅ ወደ ደቡብ መንገድ፥ ብቻውን የሚኖረው ስፍራ ወርዱ አምስት ክንድ በዙሪያው ነበር። በምዕራብም በኩል በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረ ግቢ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። በግቢውም ዙሪያ የነበረ ግንብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ ርዝመቱም ዘጠና ክንድ ነበረ። የቤተ መቅደሱንም ርዝመት መቶ ክንድ፥ የልዩውን ስፍራና ግቢውን ከግንቡ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ደግሞም በምሥራቅ በኩል የነበረውን የቤተ መቅደሱንና የልዩውን ስፍራ ወርድና ቁመት አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደኋላውም በአለው በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረውን የግቢውን ርዝመት፥ በዚህና በዚያ ከነበሩት ከግንቦቹ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ የውስጡንም መቅደስ፥ የአዳራሹንም መዛነቢያዎች ለካ። መድረኮቹ፥ መስኮቶቹና አዕማዱ፥ በስተውስጥ ያለው ክፍል ደጀ ሰላሙም በእንጨት ተለብጠው ነበር፤ በሦስቱም ዙሪያ የዐይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩ። መቅደሱም በመድረኩ አንጻር ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የዐይነ ርግብ ነበሩ፤ በደጁም ላይ እስከ ውስጠኛው ክፍል ድረስ፥ በውጭም ግንቡ ሁሉ ውስጡም፥ ውጭውም ዙሪያውን ተለብጦ ነበር። ኪሩቤልና የዘንባባው ዛፎች ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባውም ዛፍ ከኪሩብና ከኪሩብ መካከል ነበረ፤ ለእያንዳዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው። በአንድ ወገን ወደ አለው የዘንባባ ዛፍ የሰው ፊት ይመለከት ነበር፤ በሌላውም ወገን ወደ አለው ዘንባባ የአንበሳ ፊት ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተቀርጾ ነበር። ከመሬት አንሥቶ እስከ ደጁ ራስ ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ የመቅደሱ ግንብ እንደዚህ ነበረ። የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፤ የመቅደሱ ፊትም መልኩ እንደሌላው መልክ ነበረ። መሠዊያውም ቁመቱ ሦስት ክንድ፥ ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ሁለት ክንድ ሆኖ ከእንጨት ተሠርቶ ነበር፤ ማዕዘኖቹም፥ እግሩም፥ አገዳዎቹም ከእንጨት ተሠርተው ነበር፤ እርሱም፥ “በእግዚአብሔር ፊት ያለችው ገበታ ይህች ናት” አለኝ። ለመቅደሱና ለተቀደሰው ስፍራ ሁለት መዝጊያዎች ነበሩአቸው። ለእያንዳንዱ መዝጊያም ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ለአንዱ መዝጊያ ሁለት፥ ለሌላውም መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። በግንቡም ላይ በተቀረጹት ዓይነት በእነዚህ በመቅደሱ መዝጊያዎች ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በስተውጭም በአለው በደጀ ሰላሙ ፊት የእንጨት መድረክ ነበረ። በደጀ ሰላሙም በሁለቱ ወገን በዚህና በዚያ የዐይነ ርግብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎችና የእንጨቱ መድረክ እንዲሁ ነበሩ።
ሕዝቅኤል 41:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ወደ መቅደሱ አገባኝ፤ ዐምዶቹንም ለካ፤ የዐምዶቹም ወርድ በአንዱ በኩል ስድስት ክንድ፣ በሌላውም በኩል ስድስት ክንድ ነበር። የመግቢያውም በር ወርድ ዐሥር ክንድ ሲሆን፣ በግራና በቀኝ በኩል ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ወርድ ዐምስት ክንድ ነበር። ደግሞም የውስጡን መቅደስ ለካ፤ ርዝመቱ አርባ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር። ከዚያም ወደ ውስጥ ገባ፤ የመግቢያውን ዐምዶች ለካ፤ የእያንዳንዱም ወርድ ሁለት ክንድ ነበር። የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ሲሆን፣ ግራና ቀኝ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ወርድ ደግሞ ሰባት ክንድ ነበር። እርሱም የውስጠኛውን መቅደስ ርዝመት ለካ፤ ሃያ ክንድ ነበር፤ ወርዱም የውጪውን ግድግዳ ጨምሮ ሃያ ክንድ ነበር፤ እርሱም፣ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። ከዚያም የቤተ መቅደሱን ግንብ ለካ፤ ውፍረቱ ስድስት ክንድ ነው፤ በቤተ መቅደሱ ግንብ ዙሪያ ግራና ቀኝ ያለው የእያንዳንዱ ክፍል ወርድ አራት ክንድ ነበር። ግራና ቀኝ ያሉት ክፍሎች፣ ባለሦስት ደርብ ናቸው፤ በእያንዳንዱም ደርብ ላይ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ፤ በግንቡም ዙሪያ ግራና ቀኝ ያሉትን እነዚህን ክፍሎች ደግፈው የሚይዙ ተሸካሚዎች ነበሩ፤ ሆኖም ተሸካሚዎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግንብ ዘልቀው አልገቡም ነበር። በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያሉት ክፍሎች ስፋት በየደርቡ እየጨመረ የሚሄድ ነው። በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለው ሕንጻ አሠራሩ ከታች ወደ ላይ እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ፣ ወደ ላይ በተሄደ ቍጥር የክፍሎቹ ስፋት እየጨመረ የሚሄድ ነው። በመካከለኛው ደርብ በኩል አድርጎ ከታች ወደ ላይ የተዘረጋም ደረጃ አለ። ቤተ መቅደሱ ዙሪያውን ከፍ ብሎ የተሠራ መሠረት ያለው መሆኑን አየሁ፤ ይህ ግራና ቀኝ ላሉት ክፍሎች መሠረት ሲሆን፣ ርዝመቱ ስድስት ክንድ ነው፤ ይህም የዘንጉ ቁመት ነበር። በውጭ በኩል ያለው የግራና የቀኙ ክፍሎች ግንብ ውፍረት ዐምስት ክንድ ነበር፤ ክፍቱ ቦታ በቤተ መቅደሱና በካህናቱ ክፍሎች መካከል ያለ ሲሆን፣ ስፋቱ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሃያ ክንድ ነበር። ከክፍቱ ቦታ ግራና ቀኝ ወዳሉ ክፍሎች የሚያስገቡ በሮች ነበሩ። አንዱ በሰሜን በኩል ሲሆን፣ ሌላው በር ደግሞ በደቡብ በኩል ነው። ክፍቱን ቦታ ዙሪያውን የሚያገናኘው መሠረት ስፋቱ ዐምስት ክንድ ነው። በምዕራብ በኩል ከቤተ መቅደሱ ግቢ ትይዩ የሆነው ሕንጻ ወርድ ሰባ ክንድ ነበር። የሕንጻው ግንብ ውፍረት ዙሪያውን ዐምስት ክንድ ሲሆን፣ ርዝመቱ ዘጠና ክንድ ነበር። ከዚያም ቤተ መቅደሱን ለካ፤ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ የቤተ መቅደሱ ግቢና ሕንጻ ከነግንቡ ደግሞ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። በምሥራቅ በኩል የቤተ መቅደሱ ግቢ ስፋት፣ ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን ስፍራ ጨምሮ አንድ መቶ ክንድ ነበር። ከዚያም ከቤተ መቅደሱ በስተጀርባ ከግቢው ትይዩ ያለውን ሕንጻ ለካ፤ ይህም በግራና በቀኝ ያሉትን መተላለፊያዎች የሚጨምር ሲሆን፣ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ነበር። የውጩ መቅደስና የውስጡ መቅደስ ከአደባባዩ ትይዩ ያለው መተላለፊያ በረንዳ፣ እንዲሁም መድረኮቹና ጠበብ ያሉት መስኮቶች፣ በሦስቱም ዙሪያ ያሉት መተላለፊያዎች፣ ከመድረኩ በላይና ራሱ መድረኩም ጭምር ሁሉም በዕንጨት ተለብዶ ነበር። ወለሉ፣ እስከ መስኮቶቹ ያለው ግንብና መስኮቶቹ ተለብደዋል። ከውስጡ መቅደስ መግቢያ በላይ ያለው ውስጡና ውጩ እንዲሁም በውስጡ መቅደስና በውጩ መቅደስ መካከል ያለው ሁሉ ዙሪያውን ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባ ዛፎቹ የተቀረጹት በኪሩብና በኪሩብ መካከል ነበር። እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው፤ የሰው ፊት ያለው ኪሩብ በአንድ በኩል ወዳለው ዘንባባ የዞረ ሲሆን፣ የአንበሳ ፊት ያለውም በሌላ በኩል ወዳለው ዘንባባ ዞሮ ነበር። ሁሉም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ላይ ተቀርጸው ነበር። ከወለሉ አንሥቶ ከመግቢያው በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ፣ የውስጡ መቅደስ የውጭ ግድግዳ ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጿል። የውስጡ መቅደስ በር መቃን ባለአራት ማእዘን ነበር፤ ከቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ለፊት ያለው በር እንዲሁ ባለአራት ማእዘን ነበር። ሦስት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ፣ ሁለት ክንድ ርዝመት ያለው የዕንጨት መሠዊያ ነበር፤ ማእዘኖቹ፣ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከዕንጨት የተሠሩ ነበሩ። ሰውየውም፣ “ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያለች ገበታ ናት” አለኝ። የውስጡ መቅደስና ቅድስተ ቅዱሳኑ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት በር አላቸው፤ እያንዳንዱ በር መካከሉ ላይ በመታጠፊያ የተያያዙ መዝጊያዎች አሉት። በግንቦቹ ላይ እንዳለው ሁሉ በውስጡ መቅደስ በሮችም ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸዋል፤ በመተላለፊያ በረንዳውም ፊት ለፊት የዕንጨት መዝጊያ ተንጠልጥሏል። በመተላለፊያ በረንዳውም ግራና ቀኝ ግንብ ላይ የዘንባባ ዛፍ ቅርጽ ያለባቸው ጠባብ መስኮቶች ነበሩ። ግራና ቀኝ ያሉት ክፍሎችም በደረጃው በኩል የሚሸፍን ጣራ ነበራቸው።
ሕዝቅኤል 41:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። የመግቢያውም ወርድ አሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበሩ፥ ርዝመቱንም አርባ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ውስጥም ገባ፥ የመግቢያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፥ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ በዚህ ወገን ሰባት ክንድ በዚያም ወገን ሰባት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ፊት ርዘመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና፦ ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው አለኝ። የመቅደሱንም ግንብ ስድስት ክንድ አድርጎ፥ በመቅደሱም ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በመቅደሱም ግንብ ዙሪያ ደገፋዎች ይሆኑ ዘንድ አረፍቶች ነበሩ፥ በመቅደሱም ግንብ ውስጥ ደገፉዎች አልነበሩም። በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፥ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። ለመቅደሱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፥ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፥ በመቅደሱም ጓዳዎች አጠገብ የቀረ አንድ ባዶ ስፍራ ነበረ። በዚህም በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል የጓዳዎች መግቢያ ነበረ የባዶውም ስፍራ ወርድ በዙሪያ አምስት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ ልዩ ስፍራ ነበረ። በምዕራብም በኩል በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረ ግቢ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። በግቢውም ዙሪያ የነበረ ግንብ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱም ዘጠና ክንድ ነበረ። የመቅደሱንም ርዝመት መቶ ክንድ፥ የልዩውን ስፍራና ግቢውን ከግንቡ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ደግሞም በምሥራቅ በኩል የነበረውን የመቅደሱንና የልዩውን ስፍራ ወርድ አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ኋላውም ባለው በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረውን የግቢውን ርዝመት በዚህና በዚያም ከነበሩት ከግንቦቹ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። መድረኮቹ፥ መቅደሱና በስተ ውስጥ ያለው ክፍል ደጀ ሰላሙም በእንጨት ተለብጠው ነበር፥ በሦስቱም ዙሪያ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩ። መቅደሱም በመድረኩ አንጻር ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፥ መስኮቶቹም የዓይነ ርግብ ነበሩ፥ በደጁም ላይ እስከ ውስጠኛው ክፍል ድረስ፥ በውጭም ግንቡ ሁሉ ውስጡም ውጭውም ተለብጦ ነበር። ኪሩቤልና የዘንባባው ዛፎች ተቀርጸውበት ነበር፥ የዘንባባውም ዛፎች ተቀርጸውበት ነበረ፥ የዘንባባውም ዛፍ ከኪሩብና ከኪሩብ መካከል ነበረ፥ ለእያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው። በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የሰው ፊት ይመለከት ነበር፥ በሌላውም ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የአንበሳ ፊት ይመለከት ነበር፥ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተደርጎ ነበር። ከመሬት አንሥቶ እስከ ደጁ ራስ ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱ ግንብ እንደዚህ ነበረ። የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የመቅደሱ ፊትም መልኩ እንደ ሌላው መልክ ነበረ። መሠዊያውም ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱም ሁለት ክንድ ሆኖ ከእንጨት ተሠርቶ ነበር፥ ማዕዘኖቹም እግሩም አገዳዎቹም ከእንጨት ተሠርተው ነበር፥ እርሱም፦ በእግዚአብሔር ፊት ያለችው ገበታ ይህች ናት አለኝ። ለመቅደሱና ለተቀደሰው ስፍራ ሁለት መዝጊያዎች ነበሩአቸው። ለእያንዳንዱ መዝጊያም ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፥ ለአንዱ መዝጊያ ሁለት ለሌላውም መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። በግንቡም ላይ በተቀረጹት ዓይነት በእነዚህ በመቅደሱ መዝጊያዎች ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፥ በስተ ውጭም ባለው በደጀ ሰላሙ ፊት የእንጨት መድረክ ነበረ። በደጀ ሰላሙም በሁለቱ ወገን በዚህና በዚያ የዓይነ ርግብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፥ የመቅደሱም ጓዳዎችና የእንጨቱ መድረክ እንዲሁ ነበሩ።
ሕዝቅኤል 41:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም የቤተ መቅደሱ ማእከል ወደ ሆነው የተቀደሰ ስፍራ አስገባኝ፤ ወደ እርሱ የሚወስደውንም መተላለፊያ ሲለካ የሁለቱ ጐን ትይዩ ርዝመት ስድስት ክንድ ሆነ። ወርዱም ዐሥር ክንድ ሆነ፤ በግራና ቀኝ የሚገኙትም ግንቦች የእያንዳንዱ ውፍረት አምስት ክንድ ነበር፤ የተቀደሰው ስፍራ ሲለካ ርዝመቱ አርባ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ ክንድ ሆነ። ከዚያም አልፎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ገባ፤ ወደ እርሱ የሚያስገባውንም መተላለፊያ ሲለካው ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱ ስድስት ክንድ ሆነ፤ በግራና ቀኝ የሚገኙትም ግንቦች የእያንዳንዱ ውፍረት ሰባት ክንድ ሆነ። ከመካከለኛው ክፍል ባሻገር ያለውን ውስጠኛ ክፍል ከማእዘን እስከ ማእዘን ሲለካ ርዝመቱ ኻያ ክንድ ወርዱም ኻያ ክንድ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። ያ ሰው የቤተ መቅደሱን ሕንጻ የውስጠኛ ግንብ ሲለካ ውፍረቱ ስድስት ክንድ ሆነ፤ ከዚህም ግንብ ጋር ተጠግተው በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የተሠሩና የእያንዳንዱ ወርድ አራት ክንድ የሆነ ብዙ ክፍሎች ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች አንዱን በአንዱ ላይ በመቀጠል ሦስት ፎቅ ሆነው ተሠርተው፥ እያንዳንዱ ፎቅ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩት፤ በእያንዳንዱ ፎቅ ላይ ያለው የቤተ መቅደሱ ውጫዊ ግንብ በታችኛው ካለው ፎቅና ግንብ ይልቅ የሳሳ ነበር፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በቤተ መቅደሱ ሕንጻ ላይ ሳያርፍ፥ ክፍሎቹ የተደገፉት በዚያው በዋናው ግንብ ስለ ነበር ነው። የታችኛው ግድግዳ ከፎቁ ግድግዳ የወፈረ ነው፤ ሆኖም ከውጪ ሲመለከቱት ከላይ እስከ ታች ያለው ግድግዳ እኩል ውፍረት ያለው ይመስላል። ግድግዳዎቹ ከታች ወደላይ እየሳሱ ስለሚሄዱ ወደ ላይ በተወጣ ቊጥር ክፍሎቹ እየሰፉ ይሄዳሉ። መወጣጫዎቹም ከምድር ወደ ላይኛው ፎቅ የሚወጡት በመካከለኛው ፎቅ በኩል አድርገው ነው። የቤተ መቅደሱ መሠረት ስድስት ክንድ ከፍ ያለ ነበር፤ የውጪዎቹ ክፍሎችም መሠረት በዚያው ልክ ነበር። የውጪው ክፍሎች ግድግዳ ውፍረት አምስት ክንድ ነበር፤ ከቤተ መቅደሱ ጐን ካሉት ክፍሎችና ከሚቀጥሉት ሕንጻዎች መካከል ባዶ ቦታ ነበር፤ የዚህም ባዶ ቦታ ስፋት በሃያ ክንድ ቤተ መቅደሱን ይዞር ነበር። በቤተ መቅደሱ ጐን ያሉት ክፍሎች በሮቻቸው የሚከፈቱት ወደ ባዶው ቦታ አቅጣጫ ሲሆን አንዱ በሰሜን በኩል ሌላው ደግሞ በደቡብ በኩል ይከፈታል፤ የተተወውም ባዶ ቦታ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበር። በምዕራብ በኩል በባዶው ቦታ ጫፍ አንድ ሕንጻ አለ፤ የሕንጻው ግድግዳ ውፍረት ዙሪያው አምስት ክንድ፥ ወርዱ ሰባ ክንድ፥ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነው። ያ ሰው ቤተ መቅደሱን ሲለካ አንድ መቶ ክንድ ሆኖ አገኘው፤ ከቤተ መቅደሱ በኋላ በኩል ባዶው ቦታውን አቋርጦ በስተ ምዕራብ እስካለው የሕንፃው መጨረሻ ድረስ ሲለካ በአንድነት ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። ከቤተ መቅደሱም በምሥራቅ በኩል ባለው በር ፊት ለፊት ያለው ርዝመት በሁለቱም አቅጣጫ ያሉትን ክፍት ቦታዎች ጨምሮ መቶ ክንድ ሆነ፤ በሁለቱም በኩል ያሉትን መተላለፊያዎች ጨምሮ በምዕራብ በኩል ያለውን የሕንጻውን ርዝመት ሲለካው አንድ መቶ ክንድ ሆነ። የቤተ መቅደሱ መተላለፊያ፥ ቅዱሱ ስፍራና ወደ ውስጥ ዘልቆ የሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን፥ ሦስቱም ወደ ውስጥ ገባ ያሉ በዙሪያቸው ክፈፍ ያሉአቸው መስኮቶች ነበሩአቸው፤ ግድግዳዎቻቸውም ከወለሉ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት የተለበዱ ነበሩ፤ የመስኮቶቹ መዝጊያዎችም በዚሁ የተሠሩ ነበሩ። እንዲሁም በውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ የውስጥ ክፍል የሚያስገባው ከበር በላይ ያለው ስፍራም ተለብዶ ነበር፤ በውስጠኛውና በመካከለኛው ክፍል ያሉት ዙሪያ ግድግዳዎች ቅርጽ ባለው መለበጃ የተለበዱ ነበሩ። በመለበጃውም ላይ ያለው ቅርጽ የዘንባባ ዛፎችና የኪሩቤል ስዕል ነበር፤ በክፍሉም ዙሪያ የዘንባባና የኪሩቤል ሥዕሎች ተሰባጥረው ተስለውበታል፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት፤ በአንድ በኩል የሰው ፊት ቅርጽ ያለው ወደ ዘንባባው ሲመለከት፥ በሌላም አቅጣጫ የደቦል አንበሳ ቅርጽ ያለው ወደ ዘንባባው ዛፍ ይመለከት ነበር። እነርሱም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ተቀርጸው ነበር። ከወለሉ አንሥቶ ከበሮቹ በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ በግድግዳዎቹ ላይ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱም የበር መቃኖች ቅርጽ ሁሉ እኩልነት ያለው አራት ማእዘን ነበር። በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ፊት ለፊት፥ ከእንጨት የተሠራ መሠዊያ የሚመስል ነገር ይታይ ነበር፤ እርሱም እኩልነት ያለው አራት ማእዘን ሲሆን፥ እያንዳንዱ ማእዘን ሁለት ክንድ ነበር፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበር፤ የማእዘን መደገፊያ ምሰሶዎቹ፥ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ ያም ሰው “ይህ በእግዚአብሔር ፊት የሚገኝ ጠረጴዛ ነው” አለኝ። የተቀደሰው ቦታና ቅድስተ ቅዱሳኑ ድርብ መዝጊያዎች አሉአቸው። እያንዳንዱ መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት፤ ይህም ማለት ለያንዳንዱ መዝጊያ በመግፋት ወይም በመሳብ በሁለት በኩል የሚከፈቱ ሁለት ሳንቃዎች ማለት ነው። በግድግዳዎቹ ላይ እንደተቀረጸው በተቀደሰው ስፍራ በር ላይም ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ተቀርጸው ነበር። በመግቢያው ክፍል ፊት ለፊት በስተውጪ ከእንጨት የተሠራ አጎበር ነበር። በመግቢያው ክፍል ግድግዳዎች፥ በሁለቱም በኩል ወደ ውስጥ ገባ ያሉ መስኮቶች የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ነበሩ።
ሕዝቅኤል 41:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የድንኳኑን አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። የመግቢያው ወርድ ዐሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያው መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያ ወገን ደግሞ አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱን አርባ ክንድ ወርዱን ደግሞ ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ውስጥም ገብቶ የመግቢያውን ዓምድ ወርድ ሁለት ክንድ፥ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ ሰባት ክንድ ነበረ። በመቅደሱ ፊት ያለውን ርዝመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና፦ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። የቤቱን ግንብ ስድስት ክንድ፥ በቤቱ ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ ሆነው የተሠሩ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ላይ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በቤቱ ግንብ ውስጥ የተደገፉ ስላልነበሩ፥ ቤቱ በዙሪያው ላሉት ጓዳዎች ያለው ግንብ ውስጥ እንዲደገፉ ግንቡ ውስጥ ገቡ። በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። ቤቱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በቤቱ ጓዳዎች አጠገብ የቀረ ባዶ ስፍራ ነበረ። በቤቱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ በጓዳዎቹ መካከል ባዶ ስፍራ ነበረ። የጓዳዎቹም መግቢያ በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል ነበረ፤ የባዶውም ስፍራ ወርድ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበረ። በባሕር መንገድ በኩል በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረው ሕንጻ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። የሕንጻው ግንብ ዙሪያ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነበረ። ቤቱንም ለካው፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ሆነ፥ የተለየው ስፍራ፥ ሕንጻውና ግንቡ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። የቤቱና በምሥራቅ በኩል የነበረው የተለየው ስፍራ ስፋት አንድ መቶ ክንድ ሆነ። ወደ ኋላውም ባለው በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረውን የሕንጻውን ርዝመት በዚህና በዚያ የነበሩትን መተላለፊያዎች ጨምሮ ለካ፥ አንድ መቶ ክንድ ነበር። የቤተ መቅደሱ ውስጠኛው ክፍል፥ የአደባባዩ መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያዎች፥ ጠባቦቹ መስኮቶች፥ በዙሪያቸው የነበሩ ሦስት መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያ ዙሪያውን ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የተሸፈኑ ነበሩ፤ ከበሩ በላይ እስከ ውስጠኛው ቤት ድረስ፥ በዙሪያውም የነበረው ግንብ ሁሉ ውጭውም ውስጡም ተለካ። በኪሩቤልና በዘንባባ ዛፎች የተሠራ ነበር፤ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የዘንባባ ዛፍ ነበረ፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት። የሰው ፊት በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፥ የአንበሳ ፊት ደግሞ በሌላው ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተቀርጾ ነበር። ከመሬት አንሥቶ እስከ መግቢያው ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱም ግንብ እንደዚህ ነበረ። የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የተቀደሰው ሥፍራም የፊት ለፊት ገፅታው እንዲሁ ነበረ። ከእንጨት የተሠራው መሠዊያ ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ነበር፥ ማዕዘኖቹ፥ እግሩና ግድግዳው ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ እርሱም፦ “ይህ በጌታ ፊት ያለ ገበታ ነው” አለኝ። መቅደሱና የተቀደሰው ስፍራ ሁለት በሮች ነበሩአቸው። እያንዳንዱ በር ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ አንዱ በር ሁለት ሌላውም በር ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። በእነርሱም ላይ፥ በመቅደሱ በሮች ላይ በግንቡ ላይ እንደተቀረጸው ዓይነት ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በውጭ ባለው መተላለፊያ ፊት ወፍራም እንጨት ነበረ። በመተላለፊያው በዚህና በዚያ ወገን ጠባብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎች ወፍራም ነበሩ።