ወደ መቅደሱም አገባኝ፤ የግንቡንም አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ፥ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። የመግቢያውም ወርድ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የመግቢያውም መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ፥ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱንም አርባ ክንድ፥ ወርዱንም ሃያ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ውስጥም ገባ፤ የመግቢያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፤ የመግቢያውም ግንብ ወርድ በዚህ ወገን ሰባት ክንድ፥ በዚያም ወገን ሰባት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ፊት ርዝመቱን አርባ ክንድ፥ ወርዱንም ሃያ ክንድ አድርጎ ለካና፥ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። የመቅደሱንም ግንብ ስድስት ክንድ፥ በመቅደሱም ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ በሦስት ደርብ ነበሩ፤ በእያንዳንዱም ደርብ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በመቅደሱም ግንብ ዙሪያ ደገፋዎች ይሆኑ ዘንድ አረፍቶች ነበሩ፤ ከመቅደሱ ግንብ ጋር ግንአልተያያዙም ነበር። በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው፥ ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ሦስተኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። ለመቅደሱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ወርድ አምስት ክንድ ነበረ፤ በመቅደሱም ጓዳዎች አጠገብ የቀረ አንድ ባዶ ስፍራ ነበረ። በዕቃ ቤቶቹም መካከል ወርዱ በቤቱ ዙሪያ ሁሉ ሃያ ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም መግቢያ ብቻውን ወደሚኖረው ስፍራ ነበረ፤ አንዱ ደጅ ወደ ሰሜን መንገድ፤ አንዱም ደጅ ወደ ደቡብ መንገድ፥ ብቻውን የሚኖረው ስፍራ ወርዱ አምስት ክንድ በዙሪያው ነበር። በምዕራብም በኩል በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረ ግቢ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። በግቢውም ዙሪያ የነበረ ግንብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ ርዝመቱም ዘጠና ክንድ ነበረ። የቤተ መቅደሱንም ርዝመት መቶ ክንድ፥ የልዩውን ስፍራና ግቢውን ከግንቡ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ደግሞም በምሥራቅ በኩል የነበረውን የቤተ መቅደሱንና የልዩውን ስፍራ ወርድና ቁመት አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደኋላውም በአለው በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረውን የግቢውን ርዝመት፥ በዚህና በዚያ ከነበሩት ከግንቦቹ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ የውስጡንም መቅደስ፥ የአዳራሹንም መዛነቢያዎች ለካ። መድረኮቹ፥ መስኮቶቹና አዕማዱ፥ በስተውስጥ ያለው ክፍል ደጀ ሰላሙም በእንጨት ተለብጠው ነበር፤ በሦስቱም ዙሪያ የዐይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩ። መቅደሱም በመድረኩ አንጻር ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የዐይነ ርግብ ነበሩ፤ በደጁም ላይ እስከ ውስጠኛው ክፍል ድረስ፥ በውጭም ግንቡ ሁሉ ውስጡም፥ ውጭውም ዙሪያውን ተለብጦ ነበር። ኪሩቤልና የዘንባባው ዛፎች ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባውም ዛፍ ከኪሩብና ከኪሩብ መካከል ነበረ፤ ለእያንዳዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው። በአንድ ወገን ወደ አለው የዘንባባ ዛፍ የሰው ፊት ይመለከት ነበር፤ በሌላውም ወገን ወደ አለው ዘንባባ የአንበሳ ፊት ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተቀርጾ ነበር። ከመሬት አንሥቶ እስከ ደጁ ራስ ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ የመቅደሱ ግንብ እንደዚህ ነበረ። የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፤ የመቅደሱ ፊትም መልኩ እንደሌላው መልክ ነበረ። መሠዊያውም ቁመቱ ሦስት ክንድ፥ ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ሁለት ክንድ ሆኖ ከእንጨት ተሠርቶ ነበር፤ ማዕዘኖቹም፥ እግሩም፥ አገዳዎቹም ከእንጨት ተሠርተው ነበር፤ እርሱም፥ “በእግዚአብሔር ፊት ያለችው ገበታ ይህች ናት” አለኝ። ለመቅደሱና ለተቀደሰው ስፍራ ሁለት መዝጊያዎች ነበሩአቸው። ለእያንዳንዱ መዝጊያም ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ለአንዱ መዝጊያ ሁለት፥ ለሌላውም መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። በግንቡም ላይ በተቀረጹት ዓይነት በእነዚህ በመቅደሱ መዝጊያዎች ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በስተውጭም በአለው በደጀ ሰላሙ ፊት የእንጨት መድረክ ነበረ። በደጀ ሰላሙም በሁለቱ ወገን በዚህና በዚያ የዐይነ ርግብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎችና የእንጨቱ መድረክ እንዲሁ ነበሩ።
ትንቢተ ሕዝቅኤል 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሕዝቅኤል 41:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች