ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የድንኳኑን አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። የመግቢያው ወርድ ዐሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያው መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያ ወገን ደግሞ አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱን አርባ ክንድ ወርዱን ደግሞ ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ። ወደ ውስጥም ገብቶ የመግቢያውን ዓምድ ወርድ ሁለት ክንድ፥ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ ሰባት ክንድ ነበረ። በመቅደሱ ፊት ያለውን ርዝመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና፦ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። የቤቱን ግንብ ስድስት ክንድ፥ በቤቱ ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ ሆነው የተሠሩ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ላይ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በቤቱ ግንብ ውስጥ የተደገፉ ስላልነበሩ፥ ቤቱ በዙሪያው ላሉት ጓዳዎች ያለው ግንብ ውስጥ እንዲደገፉ ግንቡ ውስጥ ገቡ። በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። ቤቱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ። የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በቤቱ ጓዳዎች አጠገብ የቀረ ባዶ ስፍራ ነበረ። በቤቱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ በጓዳዎቹ መካከል ባዶ ስፍራ ነበረ። የጓዳዎቹም መግቢያ በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል ነበረ፤ የባዶውም ስፍራ ወርድ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበረ። በባሕር መንገድ በኩል በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረው ሕንጻ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። የሕንጻው ግንብ ዙሪያ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነበረ። ቤቱንም ለካው፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ሆነ፥ የተለየው ስፍራ፥ ሕንጻውና ግንቡ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። የቤቱና በምሥራቅ በኩል የነበረው የተለየው ስፍራ ስፋት አንድ መቶ ክንድ ሆነ። ወደ ኋላውም ባለው በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረውን የሕንጻውን ርዝመት በዚህና በዚያ የነበሩትን መተላለፊያዎች ጨምሮ ለካ፥ አንድ መቶ ክንድ ነበር። የቤተ መቅደሱ ውስጠኛው ክፍል፥ የአደባባዩ መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያዎች፥ ጠባቦቹ መስኮቶች፥ በዙሪያቸው የነበሩ ሦስት መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያ ዙሪያውን ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የተሸፈኑ ነበሩ፤ ከበሩ በላይ እስከ ውስጠኛው ቤት ድረስ፥ በዙሪያውም የነበረው ግንብ ሁሉ ውጭውም ውስጡም ተለካ። በኪሩቤልና በዘንባባ ዛፎች የተሠራ ነበር፤ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የዘንባባ ዛፍ ነበረ፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት። የሰው ፊት በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፥ የአንበሳ ፊት ደግሞ በሌላው ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተቀርጾ ነበር። ከመሬት አንሥቶ እስከ መግቢያው ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱም ግንብ እንደዚህ ነበረ። የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የተቀደሰው ሥፍራም የፊት ለፊት ገፅታው እንዲሁ ነበረ። ከእንጨት የተሠራው መሠዊያ ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ነበር፥ ማዕዘኖቹ፥ እግሩና ግድግዳው ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ እርሱም፦ “ይህ በጌታ ፊት ያለ ገበታ ነው” አለኝ። መቅደሱና የተቀደሰው ስፍራ ሁለት በሮች ነበሩአቸው። እያንዳንዱ በር ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ አንዱ በር ሁለት ሌላውም በር ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። በእነርሱም ላይ፥ በመቅደሱ በሮች ላይ በግንቡ ላይ እንደተቀረጸው ዓይነት ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በውጭ ባለው መተላለፊያ ፊት ወፍራም እንጨት ነበረ። በመተላለፊያው በዚህና በዚያ ወገን ጠባብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎች ወፍራም ነበሩ።
ትንቢተ ሕዝቅኤል 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሕዝቅኤል 41:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች