ሐዋርያት ሥራ 24:1-16
ሐዋርያት ሥራ 24:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት። ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስትመሰገን አግኝተናታል። ነገር ግን ነገር እንዳላበዛብህ በአጭሩ ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። ይህን ሰው ሲሳደብና ወንጀል ሲሠራ፥ አይሁድንም ሁሉ በየሀገሩ ሲያውክ፥ ናዝራውያን የተባሉት ወገኖች የሚያስተምሩትንም ክህደት ሲያስተምር አግኝተነዋል። ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም ልንፈርድበት ፈልገን ነበር። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ጭንቅ ከእጃችን ነጥቆ ወደ አንተ ላከው። ከሳሾቹንም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዛቸው፤ የከሰስንበትንም ነገር ሁሉ መርምረህ ከእርሱ ልትረዳ ትችላለህ።” አይሁድም፥ “እውነት ነው፤ እንዲሁ ነው” ብለው መለሱ። ሀገረ ገዢውም እንዲናገር ጳውሎስን ጠቀሰው፤ ጳውሎስም እንዲህ አለ፥ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ አስተዳዳሪ እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ጠባያቸውንም ታውቃለህ። አሁንም ደስ እያለኝ ክርክሬን አቀርባለሁ። እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይሆን ልታውቀው ትችላለህ፤ በምኵራብ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ቢሆን፥ በከተማም ቢሆን ሕዝብን ሳውክ፥ ከማንም ጋር ስከራከር አላገኙኝም። በሚከስሱኝ ሁሉ በፊትህ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። ነገር ግን ይህን አረጋግጥልሃለሁ፤ እኔ በሕግ ያለውን፥ በነቢያትም የተጻፈውን ሁሉ አምኜ እነርሱ ክህደት ብለው በሚጠሩት ትምህርት የአባቶችን አምላክ አመልከዋለሁ። እነርሱም ለጻድቃንና ለኃጥኣን የሙታን ትንሣኤ ይሆን ዘንድ እንደሚጠብቁ ለእኔም እንዲሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ተስፋ አለኝ። እንዲሁ እኔም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ የማታወላውል ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እጋደላለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 24:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዐምስት ቀን በኋላ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚባል ጠበቃ ጋራ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በጳውሎስም ላይ ያላቸውን ክስ ለአገረ ገዥው አቀረቡ። ጳውሎስ ተጠርቶ በቀረበ ጊዜ፣ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን አቀረበ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ፤ በአንተ ዘመን ሰላም ለብዙ ጊዜ ሰፍኖልናል፤ አርቆ አስተዋይነትህም ለዚህ ሕዝብ መሻሻልን አስገኝቶለታል፤ ክቡር ፊልክስ ሆይ፤ በየቦታውና በየጊዜው ይህን ውለታ በታላቅ ምስጋና እንቀበላለን። ነገር ግን ይበልጥ እንዳላደክምህ፣ በዐጭሩ እንድትሰማን መልካም ፈቃድህን እለምንሃለሁ። “ይህ ሰው፣ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ መካከል በሽታ ሆኖ ሁከት የሚያስነሣ፣ ደግሞም የናዝራውያን ወገን ቀንደኛ መሪ ሆኖ አግኝተነዋል። ከዚህም በላይ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር አግኝተን ያዝነው። በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር። [ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው፤ ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ።] እንግዲህ አንተ ራስህ መርምረኸው እርሱን የከሰስንበትን ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ልታረጋግጥ ትችላለህ።” አይሁድም ነገሩ እንደ ተባለው መሆኑን በመደገፍ በክሱ ተባበሩ። አገረ ገዥውም እንዲናገር በእጁ ምልክት በሰጠው ጊዜ፣ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ ፈራጅ መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ የመከላከያ መልሴን የማቀርበው በደስታ ነው። ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣሁት ከዐሥራ ሁለት ቀን በፊት መሆኑን አንተው ራስህ በቀላሉ ማረጋገጥ ትችላለህ። ከሳሾቼም በቤተ መቅደስ ከማንም ጋራ ስከራከር ወይም በምኵራብ ወይም በከተማ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ሕዝብን ሳነሣሣ አላገኙኝም። አሁንም ለተከሰስሁበት ነገር ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። ይሁን እንጂ፣ እነርሱ ኑፋቄ በሚሉት በጌታ መንገድ የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕጉ የታዘዘውንና በነቢያት የተጻፈውን ሁሉ አምናለሁ፤ ደግሞም እንደነዚህ ሰዎች ሁሉ፣ ጻድቃንና ኃጥኣን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ። ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ሁልጊዜ እጥራለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 24:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት። በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ ይከሰው ዘንድ ጀመረ እንዲህ እያለ፦ ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፥ ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ። አይሁድም ደግሞ፦ ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ። ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል፦ ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 24:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከአምስት ቀን በኋላ የካህናት አለቃው ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እነርሱም ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ ቀርበው ጳውሎስን ከሰሱ፤ ጳውሎስ ተጠርቶ በመጣ ጊዜ፥ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ አማካይነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ በመልካም አስተዳደርህም ለሕዝባችን መሻሻል ተገኝቶአል፤ እጅግ የተከበርክ ፊልክስ ይህን መልካም አድራጎትህን በየቦታውና በየጊዜው የምንቀበለው ከፍ ባለ ምስጋና ነው። አሁን ግን ጊዜህን ሳላባክን ባጭሩ የምነግርህን በቸርነትህ እንድትሰማን እለምንሃለሁ፤ ይህ ሰው መጥፎ በሽታ ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ላይ ሁከት ያስነሣል፤ ናዝራውያን ለሚባሉት መሪያቸው ነው። ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ይዘነዋል፤ [በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር፤ ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው። ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ፤] ይህን በእርሱ ላይ ያቀረብነውን ክስ ሁሉ እውነት መሆኑን አንተ ራስህ እርሱን መርምረህ ልታረጋግጥ ትችላለህ።” አይሁድ “ይህ ሁሉ ነገር እውነት ነው” እያሉ በክሱ ተስማሙ። አገረ ገዥው ፊልክስ በእጁ ጠቅሶ ጳውሎስ እንዲናገር ፈቀደለት፤ ጳውሎስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለብዙ ዓመቶች የዚህ አገር ገዢ መሆንክን ስለማውቅ ለቀረበብኝ ክስ መከላከያዬን በአንተ ፊት ሳቀርብ በጣም ደስ እያለኝ ነው፤ ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄድኩ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይበልጥ አንተ ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤ በቤተ መቅደስም ሆነ በምኲራብ ወይም በከተማ ውስጥ ከማንም ጋር ስከራከር ወይም ሕዝቡን ለሁከት ሳነሣሣ አላገኙኝም፤ አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። ነገር ግን ይህን ልገልጥልህ እወዳለሁ፤ እነርሱ አዲስ መንገድ በሚሉት የሃይማኖት ክፍል እምነት የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕግና በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈውንም ሁሉ አምናለሁ። እነርሱም ተስፋ እንደሚያደርጉት እኔም ጻድቃንና ኃጥአን ከሞት እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አደርጋለሁ። ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ዘወትር እተጋለሁ።
ሐዋርያት ሥራ 24:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዢው አመለከቱት። በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከሰው ዘንድ ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፤ ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ።” አይሁድም ደግሞ “ይህ ነገር እንዲሁ ነው፤” እያሉ ተስማሙ። ገዢውም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።