የሐዋርያት ሥራ 24:1-16
የሐዋርያት ሥራ 24:1-16 መቅካእኤ
ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዢው አመለከቱት። በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከሰው ዘንድ ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፤ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፤ ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ።” አይሁድም ደግሞ “ይህ ነገር እንዲሁ ነው፤” እያሉ ተስማሙ። ገዢውም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።

