2 ሳሙኤል 19:1-8
2 ሳሙኤል 19:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ስለ አቤሴሎም ያዝናል፤ ያለቅሳልም” ብለው ነገሩት። በዚያም ቀን፥ “ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ” ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና በዚያው ቀን ሕይወት በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለወጠ። ከሰልፍ በሸሸ ጊዜ ያፈረ ሕዝብ ተሰርቆ እንደሚገባ በዚያ ቀን ሕዝቡ ተሰርቀው ወደ ከተማ ገቡ። ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፤ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፥ “ልጄ አቤሴሎም፥ አቤሴሎም፥ ልጄ” እያለ ይጮህ ነበር። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፥ “ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ፥ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የአገልጋዮችህን ሁሉ ፊት በዚች ቀን አሳፍረሃል። አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህንም ትጠላለህ፤ አለቆችህና አገልጋዮችህ እንደማይጠቅሙህ እንደምታስብ ዛሬ ገልጠሃልና፤ አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ዛሬ እኛ ሁላችን እንሞት እንደ ነበር አውቃለሁ። ይህ በፊትህ ላንተ ቀና ነበረና። አሁንም ተነሥተህ ወጥተህ ለአገልጋዮችህ በልባቸው የሚገባ ነገር ንገራቸው። ዛሬ ወደ እነርሱ ካልወጣህ በዚች ሌሊት አንድ ሰው ስንኳ ከአንተ ጋር የሚያድር እንዳይኖር በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ከሕፃንነትህ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ ካገኘህ መከራ ሁሉ ዛሬ የምታገኝህ መከራ እንድትከፋብህ እንግዲህ አንተ ለራስህ ዕወቅ” አለው። ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ ተቀምጧል ብለው ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ በበሩ ወደ ንጉሡ ፊት ወጡ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ገብቶ ነበር።
2 ሳሙኤል 19:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ ዐዝኗል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን ዐልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው ዐብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።” ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጧል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ።
2 ሳሙኤል 19:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ። በዚያም ቀን፦ ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኅዘን ተለወጠ። ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ። ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፦ ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፥ አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፦ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፥ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ። አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፥ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፥ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል። ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፥ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደተቀመጠ ሰማ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ።
2 ሳሙኤል 19:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሥ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም ሞት በብርቱ አዝኖ በማልቀስ ላይ መሆኑን ኢዮአብ ሰማ፤ እንዲሁም ንጉሡ በልጁ ሞት ምክንያት በሐዘን ላይ መሆኑን ስለ ሰሙ ወታደሮቹ ያገኙት የድል አድራጊነት ደስታ በዚያ ቀን ወደ ሐዘን ተለወጠባቸው። ስለዚህ ከጦር ግንባር ተመልሰው ወደ ኋላ እንደሚሸሹ ወታደሮች ድምፃቸውን አጥፍተው በጸጥታ ወደ ከተማይቱ ገቡ፤ ንጉሡም ፊቱን ሸፍኖ “ልጄ ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! አቤሴሎም ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የቊባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን ሰዎች ዛሬ አሳፍረሃቸዋል፤ አንተ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የሚጠሉህን ግን ትወዳለህ! ስለ ጦር መኰንኖችህና ስለ ወታደሮችህ ሁሉ ምንም የማይገድህ መሆኑን በግልጥ አሳይተሃል፤ አቤሴሎም በሕይወት ቢኖርና እኛ ሁላችን ብንጠፋ ኖሮ እጅግ እንደምትደሰት ተገንዝቤአለሁ፤ ይልቅስ አሁን ተነሥና ወታደሮችህን አበረታታ፤ ይህንን ባታደርግ ግን ነገ ጠዋት ከእነርሱ አንዱ እንኳ ከአንተ ጋር እንደማይሆን በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ይህም በሕይወትህ ከደረሰብህ መከራ ሁሉ እጅግ የከፋ ይሆንብሃል።” ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከተቀመጠበት ተነሥቶ በመሄድ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ተከታዮቹም እዚያ መሆኑን ሰምተው ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ።
2 ሳሙኤል 19:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ በቅጽር በሩ ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም፥ ልጄን፥ ወየው ልጄን!” ይል ነበር። ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፥ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሠራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፥ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሠራዊት ዘንድ ወደ ኀዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ድምፅ ሳያሰማ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥ ልጄን! ልጄን!” እያለ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፥ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የዕቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳልሆኑ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በጌታ ስም እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያሰከትልብሃል።”