ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-8

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-8 አማ54

ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ። በዚያም ቀን፦ ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኅዘን ተለወጠ። ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ። ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፦ ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፥ አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፦ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፥ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ። አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፥ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፥ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል። ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፥ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደተቀመጠ ሰማ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ።