2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-8

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-8 መቅካእኤ

ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ በቅጽር በሩ ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም፥ ልጄን፥ ወየው ልጄን!” ይል ነበር። ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። ንጉሡ፥ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሠራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፥ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሠራዊት ዘንድ ወደ ኀዘን ተለውጦ ዋለ። በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ድምፅ ሳያሰማ ወደ ከተማ ገባ። ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥ ልጄን! ልጄን!” እያለ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፥ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የዕቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳልሆኑ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። በል አሁን ተነሥተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በጌታ ስም እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያሰከትልብሃል።”