ትንቢተ ሆሴዕ 7:1-7

ትንቢተ ሆሴዕ 7:1-7 አማ54

በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም፥ አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች። ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል። ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፥ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፥ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል። በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፥ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፥ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፥ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፥ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም።