ሆሴዕ 7:1-7
ሆሴዕ 7:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኀጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። ወንጀላቸውን አንድ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው እንደ አሰቡ ክፋታቸውን ሁሉ ዐሰብሁ፤ አሁንም ክፋታቸው ከብባቸዋለች፤ በደላቸውም በፊቴ አለች። ነገሥታቱ በክፋታቸው፥ አለቆቹም በሐሰታቸው ደስ ተሰኙ። ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉም እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቈያል። በንጉሦቻችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እነርሱም ከዋዘኞች ጋር እጆቻቸውን ዘረጉ። እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ ጋጋሪያቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፤ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም መካከል የሚጠራኝ የለም።
ሆሴዕ 7:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እስራኤልን በምፈውስበት ጊዜ፣ የኤፍሬም ኀጢአት፣ የሰማርያም ክፋት ይገለጣል። እነርሱ ያጭበረብራሉ፤ ሌቦች ቤቶችን ሰብረው ይገባሉ፤ ወንበዴዎችም በየመንገድ ይዘርፋሉ። ነገር ግን ክፉ ድርጊታቸውን ሁሉ እንደማስታውስ፣ እነርሱ አይገነዘቡም፤ ኀጢአታቸው ከብቧቸዋል፤ ሁልጊዜም በፊቴ ናቸው። “ንጉሡን በክፋታቸው፣ አለቆችንም በሐሰታቸው ያስደስታሉ። ሊጡ ቦክቶ ኩፍ እንደሚል፣ ዳቦ ጋጋሪው እሳት መቈስቈስ እስከማያስፈልገው ድረስ፣ እንደሚነድድ ምድጃ፣ ሁሉም አመንዝራ ናቸው። በንጉሣችን የበዓል ቀን፣ አለቆች በወይን ጠጅ ስካር ጋሉ፤ እርሱም ከፌዘኞች ጋራ ተባበረ። ልባቸው እንደ ምድጃ የጋለ ነው፤ በተንኰል ይቀርቡታል፤ ቍጣቸው ሌሊቱን ሙሉ ይጤሳል፤ እንደሚነድድም እሳት በማለዳ ይንበለበላል። ሁሉም እንደ ምድጃ የጋሉ ናቸው፤ ገዦቻቸውን ፈጁ፤ ንጉሦቻቸው ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም ወደ እኔ የቀረበ ማንም የለም።
ሆሴዕ 7:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም፥ አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች። ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል። ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፥ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፥ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል። በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፥ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፥ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፥ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፥ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም።
ሆሴዕ 7:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ሕዝቤን እስራኤልን ለመፈወስና እንደገናም እንዲበለጽጉ ለማድረግ በፈለግሁ ጊዜ የሕዝቡ በደልና የሰማርያ ክፋት ጐልቶ ይታያል፤ እርስ በርሳቸው ሐሰት ይናገራሉ፤ ቤት እየሰበሩ ይሰርቃሉ፤ በቡድን በቡድን ሆነው በየመንገዱ ይዘርፋሉ። ነገር ግን እኔ ይህን ሁሉ ክፋታቸውን እንደማስታውስ ከቶ አይገነዘቡም፤ ከዚህ የተነሣ በገዛ ኃጢአታቸው ተከበዋል፤ ክፉ ሥራቸው ሁሉ ከእኔ የተሰወረ አይደለም።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ንጉሡን በክፋታቸው፥ መኳንንቱን በውሸታቸው ያስደስታሉ። ሁሉ ዘማውያን ናቸው፤ ሊጡ እስኪቦካለት ድረስ ዳቦ ጋጋሪው እሳቱን መቈስቈስ እንደማያስፈልገው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። በንጉሣቸው ክብረ በዓል ቀን መኳንንቱ ብዙ የወይን ጠጅ በመጠጣት ሰክረው ታመሙ፤ ጋጋሪውም ለሚያፌዙ ሰዎች ምልክት ለመስጠት እጁን ዘረጋ። ሤራ ለመጐንጐን ልባቸው እንደ ምድጃ የጋለ ነው፤ ቊጣቸው ሌሊቱን ሙሉ ሲጤስ ያድራል፤ ሲነጋ ግን እንደሚነድ እሳት ይንበለበላል። “ሁሉም በቊጣ እንደ ምድጃ ግለው ገዢዎቻቸውን ፈጁ፤ ንጉሦቻቸውንም በየተራ አጠፉ፤ ይህም ሁሉ ሲሆን ከእነርሱ አንድ እንኳ የእኔን ርዳታ የጠየቀ የለም።”
ሆሴዕ 7:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በገላጣም ስፍራ ወንበዴ ቀምቶአልና፤ እስራኤልን በፈወስሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንደማስታውስ ልብ አላደረጉም፤ አሁንም ሥራዎቻቸው ከብበዋቸዋል፥ እነርሱም በፊቴ አሉ። ንጉሡን በክፋታቸው፥ ሹማምንቱንም በሐሰታቸው ደስ ያሰኛሉ። ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ የተለወሰውን ቡኮ እስኪቦካ ድረስ ጋጋሪ እሳቱን ሳይቆሰቁሰው እንደ ተወው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። በንጉሣችን ቀን ሹማምንቱ ከወይን ጠጅ ሞቅታ የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከፌዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። በሴራቸው ልባቸው እንደ ምድጃ ተቃጥላለችና፤ ጋጋሪያቸው ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በነጋም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ነደደ። ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም አጥፍተዋል፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወድቀዋል፤ ከእነርሱም መካከል ወደ እኔ የጮኸ የለም።