ትንቢተ ሆሴዕ 7:1-7

ትንቢተ ሆሴዕ 7:1-7 አማ05

“ሕዝቤን እስራኤልን ለመፈወስና እንደገናም እንዲበለጽጉ ለማድረግ በፈለግሁ ጊዜ የሕዝቡ በደልና የሰማርያ ክፋት ጐልቶ ይታያል፤ እርስ በርሳቸው ሐሰት ይናገራሉ፤ ቤት እየሰበሩ ይሰርቃሉ፤ በቡድን በቡድን ሆነው በየመንገዱ ይዘርፋሉ። ነገር ግን እኔ ይህን ሁሉ ክፋታቸውን እንደማስታውስ ከቶ አይገነዘቡም፤ ከዚህ የተነሣ በገዛ ኃጢአታቸው ተከበዋል፤ ክፉ ሥራቸው ሁሉ ከእኔ የተሰወረ አይደለም።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ንጉሡን በክፋታቸው፥ መኳንንቱን በውሸታቸው ያስደስታሉ። ሁሉ ዘማውያን ናቸው፤ ሊጡ እስኪቦካለት ድረስ ዳቦ ጋጋሪው እሳቱን መቈስቈስ እንደማያስፈልገው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። በንጉሣቸው ክብረ በዓል ቀን መኳንንቱ ብዙ የወይን ጠጅ በመጠጣት ሰክረው ታመሙ፤ ጋጋሪውም ለሚያፌዙ ሰዎች ምልክት ለመስጠት እጁን ዘረጋ። ሤራ ለመጐንጐን ልባቸው እንደ ምድጃ የጋለ ነው፤ ቊጣቸው ሌሊቱን ሙሉ ሲጤስ ያድራል፤ ሲነጋ ግን እንደሚነድ እሳት ይንበለበላል። “ሁሉም በቊጣ እንደ ምድጃ ግለው ገዢዎቻቸውን ፈጁ፤ ንጉሦቻቸውንም በየተራ አጠፉ፤ ይህም ሁሉ ሲሆን ከእነርሱ አንድ እንኳ የእኔን ርዳታ የጠየቀ የለም።”