ኦሪት ዘፍጥረት 31:2-21

ኦሪት ዘፍጥረት 31:2-21 አማ54

ያዕቆብም የላባን ፊት አየ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም። እግዚአብሔርም ያዕቆብን፦ ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው። ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆን አያለሁ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው። እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ። አባታችሁ ግን አታለለኝ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ እግዚአብሔር ግን ክፋን ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ። እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎቹ ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ እንዲህም ሆነ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ እነሆም በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችን የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ። የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም፦ ያዕቆብ ሆይ አለኝ እኔም፦ እነሆኝ አልሁት። እንዲህም አለኝ፦ ዓይንህን አቅንተህ እይ በበጎችን በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ። ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት፦ በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን? እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና። ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ። ያዕቆብም ተነሣ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ መንጎቹንም ሁሉ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር ራሔልም የአባትዋን ተራፌም ሰረቀም። ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ መኮብለሉን፥ አልነገረውም። እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}