መጽሐፈ ሲራክ 27
27
1በግብዝነት ኀጢአትን የሚሠሩአት ብዙዎች ናቸው፤
ገንዘቡ ይበዛለት ዘንድ የሚወድድ ሰው ግን ዐይኑን ይመልሳል።
2ችንካር በድንጋይ ግንብ መካከል እንደሚተከል፥
በመሸጥና በመግዛት መካከል ኀጢአት ትመጣለች።
3እግዚአብሔርን በመፍራት ፈጥኖ ካልተጠበቀ፥
የቤቱ ውድቀት አይዘገይም።
የሕይወት መመዘኛ
4በወንጠፍት ዐሠር ይከማቻል፤
እንዲሁም ሁሉ ሰውን ኀጢአቱ ታገኘዋለች።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እንዲሁ በኀጢአተኛ ሰው ንግግር ኀጢአት ትከማቻለች” ይላል።
5የሸክላ ዕቃን እሳት ይፈትነዋል፤
ሰውንም የልቡናው ዐሳብ ይፈትነዋል።
6ተክል የሚጠብቅ ሰው ፍሬውን ያያል፤
እንዲሁም የሰው ነገሩ የልቡናውን ፈቃድ ይገልጥበታል።
7ሰውን ሳትረዳው አታድንቀው፤
ሰውን ከሥራው የተነሣ ይፈትኑታልና።
8ጽድቅን ብትከተላት ታገኛታለህ፥
እንደ ከበረ ግምጃም ትለብሳታለህ።
9ወፍ ከዘመዱ ጋር ይኖራል፤
ጽድቅም በሚሠሯት ሰዎች ዘንድ ትኖራለች።
10አንበሳ የሚበላውን ያድናል፤
እንዲሁም ኀጢአት የሚሠሯትን ሰዎች ታድናቸዋለች።
11ጻድቅ ሰው ሁልጊዜ ጥበብን ያስተምራል፤
የሰነፍ ሰው ግን ዕውቀቱ እያደረ እንደ ጨረቃ ይጐድላል።
12በሰነፎች ዘንድ ጊዜውን ተጠበቅ፤
በብልሆች ሰዎች ዘንድ ግን ሁልጊዜ ተረዳ።
13የሰነፎች ነገር ያበሳጫል፤
ሣቃቸውም የኀጢአት ደስታ ነው።
14ብዙ መሐላን የሚምል ሰው ነገር ፀጕርን ያቆማል፤
የትዕቢተኛ ሰው ክርክርም ዦሮ ያደነቍራል።
15የትዕቢተኞች ጠብ ደም ያፋስሳል፤
ክርክራቸውም ለሚሰማቸው ሰው ድካም ነው።
የባልንጀራን ምሥጢር ማውጣት እንደማይገባ
16የባልንጀራውን ምሥጢር የሚያወጣ ሰው መታመኑን ያጠፋል፤
ከዚህም በኋላ እንደ ልቡ የሚሆን ወዳጅን አያገኝም።
17ወዳጅህን ጠብቅ፤ ከእርሱም ጋራ ተማመን፤
ምሥጢሩን ብታወጣበት ግን በኋላው አትከተለውም።
18ሰው ጠላቱን እንደሚያጠፋ፥
አንተም የወዳጅህን ወንድምነት ታጠፋለህ።
19ወፍ ከእጅህ እንደምታመልጥ፥
እንዲሁ ወዳጅህ ከአንተ ያመልጣል።
20ምዳቋ ከወጥመድ እንደምታመልጥ፥
ከአንተ አምልጦ ርቋልና ከዚህ በኋላ አትከተለውም።
21ቍስል ቢሆን ባዳኑት ነበር፤ የተሰደበንም ሰው ባስካሱት ነበር፤
የባልንጀራውን ምሥጢር የሚያወጣውን ሰው ግን ተስፋ ይቈርጡበታል።#ግሪኩ “ተስፋ ቢስ ይሆናል” ይላል።
ስለ ግብዝነት
22ክፋቱን ማስተው የሚችል የለምና፤
በዐይኑ የሚጠቅስ ሰው ልቡናው ያማረ አይሆንም።
23ለዐይንህ ግን ከንፈሩን ይመጥጥልሃል፤
በተናገርኸውም ሁሉ ያመሰግንሃል፤
ኋላ ግን በቃሉ ይወነጅልሃል፤
በተናገርኸው ቃልህም ያጠምድሃል።
24የጠላኋቸው ብዙዎች ናቸው፤
ነገር ግን እንደ እርሱ አይደሉም፤
እግዚአብሔርም እርሱን ይጠላል።
25ድንጋይን ወደ ላይ የሚወረውር ሰው በራሱ ላይ ትወርዳለች፤
የበደል ግርፋትም ቍስሉ ይታወቃል።
26ለባልንጀራው ጕድጓድ የቈፈረ ሰው፥ እርሱ በውስጡ ይወድቃል፤
ወጥመድም ያዘጋጀ ሰው ራሱ ይያዝበታል።
27ሰው ኀጢአትን ቢሠራ በእርሱ ላይ ትመለሳለች፤
ከየትም እንደምትመጣ አያውቅም።
28የትዕቢተኞች ስድባቸውና ሣቃቸው
እንደ አንበሳ ያድኑአቸዋል፤ ይበቀሉአቸዋልም።
29በጻድቅ ሰው መውደቅ ደስ የሚላቸው ሰዎች በወጥመድ ይያዛሉ፤
የሚሞቱበትም ጊዜ ሳይደርስ መቅሠፍት ያጠፋቸዋል።
30ቍጣና መዓትም የሚያስጸይፉ ናቸው፤
በኀጢአተኛ ሰውም ዘንድ ጸንተው ይኖራሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 27: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ