መጽሐፈ ሲራክ 26
26
የደግ ሴት ተግባር
1ደግ ሴትን ባሏ ያመሰግናታል፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ደግ ሚስት ያለችው ብፁዕ ነው” ይላል።
የሕይወት ዘመኑም እጥፍ ይሆናል።
2ቅን ሴት ባሏን ደስ ታሰኘዋለች፤
ዘመኑንም በሰላም ይጨርሳል።
3የደግ ሴት ዕድሏ ያማረ ነው፤
እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውንም ወደ ዕድሉ ታደርሰዋለች።
4የባለጸጋውም የድሃውም ልቡ የቀና ይሁን፤
ሁልጊዜም ፊቱ የበራ ይሁን።
ስለ ክፉ ሴት
5በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች ልቡናዬ ደነገጠብኝ፤
አራተኛውም ፊቴን አስፈራኝ፤
ይኸውም የከተማ ሁከት፥ የአሕዛብ መዶለት፥
የሐሰት ምስክር፤ እነዚህ ሁሉ ሰውን ለሞት ያደርሳሉ።
6ባሏን የምታስቀና ሴት የልብ ቍስል ናት፤ የሰውነትም ኀዘን ናት፤
በክፉ ሁሉ የምትስተካከል የምላስ ጅራፍ ናት።
7ክፉ ሴት ውልቅ ውልቅ እንደሚል፥ እንደ በሬ ቀንበር ናት፤
እርስዋንም የሚይዝ ሰው ጊንጥ እንደሚጨብጥ ሰው ነው።
8ሰካራም ሴት ታላቅ ጥፋት ናት።
ኀፍረትዋንም አትሸፍንም፤
9የሴት ዝሙትዋ በዐይኗ ይታወቃል፤
በቅንድቧም ይታወቃል።
10ስታ ራሷን እንዳታጠፋ፥
ልጅህን አጽንተህ ጠብቃት።
11ከአመንዝራ ዐይን ጠብቃት፤
ብትበድልህም አትደነቅ።
12እርስዋ የተጠማ ሰው ከቀረበው ውኃ ሁሉ እየላሰ እንደሚጠጣ፥
በዛፍም ሁሉ ሥር እንደሚያርፍ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የተጠማ መንገደኛ ምንጭ ባገኘ ጊዜ ከቀረበው ውኃ ሁሉ እንደሚጠጣ፥ አፍዋን ትከፍታለች ፤ በዛፉም ሥር ሁሉ ትቀመጣለች ፤ በፍላጻውም አቅጣጫ ሁሉ ሰገባዋን ትከፍታለች ፤” ይላል።
13ፍላጻውንም ከሰገባው እንደሚያወጣ ናትና።
የደግ ሴት በረከት
14የሴት ሞገስዋ ባሏን ደስ ያሰኛል።
15ጥበቧም አጥንቱን ያለመልመዋል።
16የዋህ ሴት የእግዚአብሔር ስጦታ ናት።
17ለብልህ ሴት ለውጥ የላትም።
18የምታፍር ሴት በበረከት ላይ በረከት ናት።
19ለትዕግሥተኛ ሴት ለውጥ የላትም።
20ፀሐይ በእግዚአብሔር ሰማይ እንደሚያበራ፥
እንደዚሁ የደግ ሴት ውበቷ ባማረ በቤቷ ውስጥ ነው።
21የተቀደሰችው መብራት በመቅረዟ ላይ እንደምታበራ፥
እንዲሁ የብልህ ሰው የመልኩ ውበት በጠባዩ ውበት ነው።
22በብር ስክተት ላይ እንደቆሙ የወርቅ ምሰሶዎች፥
በበጎ ሥራ የቆመ የደግ ሰው እግር አገባብም እንዲሁ ነው።
23በእነዚህ በሦስቱ#ግሪኩ “በእነዚህ በሁለቱ” ይላል። ነገሮች ልቡናዬ አዘነብኝ።
24ዐራተኛው#ግሪኩ “ሦስተኛው” ይላል። ግን ብስጭትን አመጣብኝ።
25እነዚህም አርበኛና ደፋር ሰው አጥቶ ሲቸገር፥
26ጠቢባን ሰዎች ሲስቱ፥
27ጽድቅን ትቶ ወደ ኀጢአት የሚመለስ ሰው ናቸው።
28እንዲህ ያለውን እግዚአብሔር በጦር ያጠፋዋል።
29አጣሪ ከኀጢአቱ በጭንቅ ይድናል፤
መሸተኛም ከበደል ተመልሶ አይጸድቅም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 26: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ