መጽሐፈ ሲራክ 23
23
ከኀጢአት ስለ መራቅ ጸሎት
1አቤቱ፥ አባቴ፥ የሕይወቴም ፈጣሪ፥
በእነርሱ ምክር አትጣለኝ፥
በእነርሱም እንዳልጠፋ አትለየኝ፤
2ልቡናዬን ማን በመከረልኝ?
ድንቍርናዬም ይተወኝ ዘንድ፥ በተናገሩብኝም ነገር ድል እንዳይነሱኝ፥ ለልቡናዬ ጥበብን ማን ባስተማራት?
3በደሌ እንዳይበዛብኝ፥ ኀጢአቴም እንዳይበረክትብኝ፥
በጠላቶችም ፊት እንዳልወድቅ፥
ጠላቶችም በእኔ ጥፋት ደስ እንዳይላቸው፥
4ጌታዬ፥ አባቴ፥ የሕይወቴ ፈጣሪ ሆይ፥
ዐይኔን የሚያስታትን ነገር አታምጣብኝ።
5መጐምጀትንም ከእኔ አርቅልኝ።
6ጥጋብ አይምጣብኝ፤ ቍንጣንም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ፍትወተ ሥጋ” ይላል። አያቀናጣኝ፤
ለክፉ ሰውም አሳልፈህ አትስጠኝ።
አንደበትን ስለ መግራት
7ልጆች ሆይ፥ የአንደበቴን ምክር ስሙኝ፤
ቃሌን የጠበቀ አይሰነካከልም፤ አንደበቱንም የጠበቀ አይወድቅም።
8ኀጢአተኛ በስንፍናው ይያዛል፤
ተሳዳቢና ትዕቢተኛም በዚሁ ይሰነካከላሉ።
9ልጄ ሆይ፥ ለአፍህ መሐላን አታስለምደው፤
በማልህም ጊዜ የቅዱሱን ስም በሐሰት አትጥራ።
10ሁልጊዜ እየተመረመረ የሚገረፍ ባሪያ ቍስሉ እንደማይደርቅ፥
እንደዚሁ ሲምል ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ስም በሐሰት የሚጠራ ሰው ከኀጢአት አይነጻም።
11መሐላን የሚያበዛ ሰው ኀጢአቱ ብዙ ነው፥
ከቤቱም መቅሠፍት አይርቅም፤
ቢያረጅም#ግሪኩ “በስሕተት ኀጢአት ቢሠራ” ይላል። ኀጢአቱ አይተወውም፤
ቸል ቢልም ኀጢአቱ እጥፍ ይሆንበታል፤
ፍዳው በቤቱ ሞልትዋልና ስለ ማለ እውነተኛ አይባልም።
12ሞትን የምታመጣው ቃል አለች፤
በያዕቆብም ርስት አትኖርም፤
ይህ ሁሉ በጻድቃን ዘንድ የለም፤ በኀጢአትም አይሰነካከሉም።
13በውስጡ ብዙ ኀጢአት አለና፥
ከአንደበትህ የመዘባበት ነገር አይውጣ።
14አባትህንና እናትህን ዐስባቸው፥
መኳንንቶችህንም አገልግል፤#ግሪኩ “በታላላቆች መካከል በተቀመጥህ ጊዜ አባትህንና እናትህን ዐስባቸው” ይላል።
በፊታቸውም አትሳት፤
ባልተወለድሁ እንዳትል፥
የተወለድህበትንም ቀን እንዳትረግም በስንፍናህ እንዳትጠላ ሁን።
15በሰው ላይ መሳለቅን የለመደ ሰው፥
መላ ሕይወቱን ብልህ አይሆንም።
ስለ ዝሙት ኀጢአት
16ኀጢአትን የሚያመጧት ሁለት ናቸው፤
ሦስተኛው ግን ሞትን ያመጣል፤
ቍጡ ሰውነት እንደሚቃጠል እሳት ናት፤
እስክታሰጥመውም ድረስ አትበርድም፤
በሰውነቱም የሚሰስን ሰው እሳትን እስኪያቀጣጥላት ድረስ አይተውም።
17ለሴሰኛ ሰው እህሉ ሁሉ ይጣፍጠዋል፤
እስኪሞትም ድረስ አያርፍም።
18ሚስቱን ትቶ የሚሄድ ሰው፥
በልቡ “ጊዜው ጨለማ ነው፤ የሚያየኝ የለም፤ አጥር ይጋርደኛል፤
ከዚህ በኋላ ምን እፈራለሁ? የሚያውቀኝም የለም፤
ልዑልም ኀጢአቴን ይዘነጋልኛል፤ አያስብብኝምም” ይላል።
19ነገር ግን እንዳያየው የሰው ዐይንን ይፈራል፤
የእግዚአብሔርም ዐይን ከፀሐይ መቶ ሺህ ጊዜ እንዲበራ፥
የሰውንም ሥራ ሁሉ እንደሚያይ፥
ተሰውሮ የሚሠራንም ሥራ ሁሉ እንደሚያውቅ አያውቅም።
20ሁሉም ከመፈጠሩ በፊት በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው፤
ከጨረሰም በኋላ እንዲህ ያደርገዋል።
21በከተማም መካከል ይበቀለዋል፤
ባልጠረጠረበትም ቦታ ያጠፋዋል።
22ባሏን ትታ የምትሄድ ሴት እንዲሁ ናት፤
ከሌላ ወንድ ልጅን ትወልዳለች።
23በእግዚአብሔር አንዲት ክህደት አደረገች፤
ሁለተኛም ባሏን ከዳችው፥
ሦስተኛም በሴሰኝነትዋ ሰረቀች፤
ከሌላ ወንድም ልጅን ወለደች።
24እንዲህ ያለችው ሴት ቷረዳለች፤
በልጆችዋም ትገረፋለች።
25ዘሮችዋ ይጠፋሉ፤
ቅርንጫፎችዋም አያፈሩም።
26ስም አጠራሯም የተረገመ ይሆናል፤
ለቤቷም መርገምን ታወርሳለች፤
መርገምዋና ውርደቷ ለዘለዓለሙ አይጠፋም።
27ያያት ሁሉ እግዚአብሔርን ከመፍራት የሚበልጥ፥
የእግዚአብሔርንም ሕግ ከመጠበቅ የሚጣፍጥ እንደሌለ ያውቃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 23: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ