መጽሐፈ ሲራክ 17
17
1እግዚአብሔር ሰውን ከምድር ፈጠረው፥
ዳግመኛም ወደ ምድር ይመልሰዋል።
2ዓመታትንና ቀናትን በቍጥር ሰጣቸው፤
በውስጧም ያለውን ሁሉ አስገዛቸው።
3ለእየራሳቸው ኀይልን አሳደረባቸው፤
በምሳሌውም ፈጠራቸው።
4ፍጥረቱ ሁሉ እንዲፈሩአቸው አደረገ።
5አውሬዎችንና ወፎችንም እንዲገዟቸው አደረገ።
6ቃልንና አንደበትን፥ ዐይንና ጆሮን፥
የሚያስቡበት ልቡናንም ሰጣቸው።
7ጥበብን ማወቅንም አጠገባቸው፤
ክፉንና በጎንም አሳያቸው።
8የሥራውን ገናናነትና መፈራቱንም ያሳያቸው ዘንድ፥
በልቡናቸው ፍርሀትን አሳደረባቸው።
9ቅዱስ ስሙን ያመሰግኑት ዘንድ።
10የሥራውንም ገናናነት ይናገሩ ዘንድ፥
11ጥበብን ሰጣቸው፤
የሚያድናቸው ሕጉንም አወረሳቸው።
12የዘለዓለም መሐላንም ተማማላቸው፤
ፍርዱንም ነገራቸው።
13ዐይኖቻቸውም የጌትነቱን ገናናነት አዩ።
14የጌትነቱንም ቃል ጆሮቻቸው ሰሙ፥
15ከኀጢአት ሁሉ ተጠበቁ አላቸው፤
ሁሉንም ባልጀራችሁን ውደዱ ብሎ አዘዛቸው።
16መንገዳቸውም ሁልጊዜ በፊቱ ነው፥
ከዐይኖቹም የሚሰወሩበት የላቸውም።
17ለአሕዛብ ሁሉ ነገሥታትን አነገሠላቸው።
18እስራኤል ግን የእግዚአብሔር ክፍል ሆነ።
19ሥራቸውም ሁሉ በፊቱ እንደ ፀሐይ ነው፤
ዐይኖቹም ሁልጊዜ መንገዳቸውን ያያሉ።
20ኀጢአታቸውም ከእርሱ አልተሰወረችም፤
በደላቸውም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ነው።
21የሰው ምጽዋቱ ከእርሱ ጋራ እንደ ማኅተም ነው።
22የሰው ዋጋው እንደ ዐይን ብሌን ትጠበቅለታለች።
23ኋላ ተመልሶ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል፤
የኀጢአታቸውንም ፍዳ ወደ ራሳቸው ይመልሳል።
24ነገር ግን ንስሓ የሚገቡበትን መንገድ ሰጣቸው፤
ተስፋ የቈረጡ ሰዎችንም ደስ ያሰኛቸዋል።
የንስሓ ጥሪ
25ወደ እግዚአብሔር ተመለስ፥
ኀጢአትንም ተዋት በፊቱም ጸልይ፥
ለበደልህም ንስሓ ግባ፤
26ከበደልህም ወደ እግዚአብሔር ተመለስ፤
ኀጢአትን ሁሉ ጥላ ፈቃዱንም አድርግ።#“ፈቃዱንም አድርግ” የሚለው በግሪኩ የለም።
27በሕይወት ሳሉ እንደሚገዙለት ሰዎች፥
ልዑልን በመቃብር የሚያመሰግነው ማንነው?
28የሞተ ሰውን ግን ንስሓ እንደ ኢምንት አለፈው፤
በሕይወትህ ደስ እያለህ እግዚአብሔርን አመስግነው።
29የእግዚአብሔር ቸርነቱ ታላቅ ነውና፤
የሚገዙለትን ሰዎች ይቅር ይላቸዋል።
30ሰው ሟች ስለ ሆነ፥
ሁሉ በሰው ዘንድ ሊሆን አይችልም።
31ከፀሐይ የሚበራ ምን አለ? እርሱም እንኳ ያልፋል።
ደማዊና ሥጋዊም ክፉ ነገርን ያስባል።
32እርሱ የሰማይን ምጥቀት ኀይል ያውቃል፥
ሰው ሁሉ ግን አመድና ትቢያ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 17: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ