መዝሙረ ዳዊት 72:1-20
መዝሙረ ዳዊት 72:1-20 አማ2000
ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እጅግ ቸር ነው። እኔ ግን እግሮች ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ጥቂት ቀረ። የዐመፀኞችን ሰላም አይቼ በኃጥኣን ላይ ቀንቼ ነበርና። ለሞታቸው እረፍት የለውምና፤ ለመቅሠፍታቸውም ኀይል የለውምና፤ በድካምም ጠላት አልሆኑም። ከሰው ጋርም አልተገረፉም። ስለዚህም ትዕቢት ያዛቸው፤ ኀጢአታቸውንና በደላቸውን ተጐናጸፉአት። መቅን ከቅልጥም እንደሚወጣ ኀጢአታቸው ይወጣል። ልባቸውም ከትዕቢት አለፈ። ዐስበው ከንቱ ነገርን ተናገሩ። በአርያምም ዐመፃን ተናገሩ። አፋቸውንም በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ላይ ተመላለሰ። ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤ “እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በአርያምስ በውኑ የሚያውቅ አለን?” ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ኃጥኣን ደስ ይላቸዋል፤ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያጸኗታል፤ እንዲህም አልሁ፥ “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁአትን?” እጆቼንም በንጽሕና አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። አውቅም ዘንድ ተቀበልኸኝ፥ ይህ ግን በፊቴ ድካም ነው። ፍጻሜአቸውን አውቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ነገር ግን ስለ ሽንገላቸው አቈየሃቸው፥ በመነሣታቸውም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ፥ ስለ ኀጢአታቸውም ጠፉ። ከእንቅልፍ እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ በከተማህ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።

