መዝሙር 72:1-20
መዝሙር 72:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እጅግ ቸር ነው። እኔ ግን እግሮች ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ጥቂት ቀረ። የዐመፀኞችን ሰላም አይቼ በኃጥኣን ላይ ቀንቼ ነበርና። ለሞታቸው እረፍት የለውምና፤ ለመቅሠፍታቸውም ኀይል የለውምና፤ በድካምም ጠላት አልሆኑም። ከሰው ጋርም አልተገረፉም። ስለዚህም ትዕቢት ያዛቸው፤ ኀጢአታቸውንና በደላቸውን ተጐናጸፉአት። መቅን ከቅልጥም እንደሚወጣ ኀጢአታቸው ይወጣል። ልባቸውም ከትዕቢት አለፈ። ዐስበው ከንቱ ነገርን ተናገሩ። በአርያምም ዐመፃን ተናገሩ። አፋቸውንም በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ላይ ተመላለሰ። ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤ “እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በአርያምስ በውኑ የሚያውቅ አለን?” ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ኃጥኣን ደስ ይላቸዋል፤ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያጸኗታል፤ እንዲህም አልሁ፥ “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁአትን?” እጆቼንም በንጽሕና አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። አውቅም ዘንድ ተቀበልኸኝ፥ ይህ ግን በፊቴ ድካም ነው። ፍጻሜአቸውን አውቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ነገር ግን ስለ ሽንገላቸው አቈየሃቸው፥ በመነሣታቸውም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ፥ ስለ ኀጢአታቸውም ጠፉ። ከእንቅልፍ እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ በከተማህ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።
መዝሙር 72:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍትሕን ለንጉሥ፣ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ ዐድል፤ እርሱም ሕዝብህን በጽድቅ ይዳኛል፤ ለተቸገሩትም በትክክል ይፈርዳል። ተራሮች ብልጽግናን፣ ኰረብቶችም የጽድቅን ፍሬ ለሕዝቡ ያመጣሉ። ለተቸገረው ሕዝብ ይሟገታል፤ የድኾችን ልጆች ያድናል፤ ጨቋኙንም ያደቅቀዋል። ፀሓይ እስካለች ድረስ፣ ጨረቃም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ ይወርዳል፤ እንደ ካፊያም ምድርን ያረሰርሳል። በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል። የበረሓ ዘላኖች በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐፈር ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት፣ ግብር ያመጡለታል፤ የዐረብና የሳባ ነገሥታት፣ እጅ መንሻ ያቀርባሉ። ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙለታል። ድኻው በጮኸ ጊዜ፣ ችግረኛውና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ድኾችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በርሱ ፊት ክቡር ነው። ዕድሜው ይርዘም! ወርቅም ከሳባ ይምጣለት፤ ዘወትር ይጸልዩለት፤ ቀኑንም ሙሉ ይባርኩት። በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ። ፍሬው እንደ ሊባኖስ ይንዠርገግ፤ በከተማ ያለውም እንደ ሜዳ ሣር እጅብ ብሎ ይውጣ። ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ። ሕዝቦች ሁሉ በርሱ ይባረኩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው። ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ፤ ምድርም ሁሉ በክብሩ ትሞላ። አሜን፤ አሜን። የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎት እዚህ ላይ ተፈጸመ።
መዝሙር 72:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ለንጉሡ ትክክለኛ ፈራጅነትን ለንጉሡም ልጅ ጽድቅህን ስጥ። በዚህ ዐይነት ሕዝብህን በትትክል ያስተዳድራል፤ ለጭቊኖችህም በትክክል ይፈርዳል። ተራራዎች ብልጽግናን፥ ኰረብቶችም የጽድቅ ፍሬን ለሕዝብ ያስገኙ። በሕዝቡ መካከል ለተጨቈኑት ፍርድን ይስጥ፤ ችግረኞችንም ይርዳ፤ ጨቋኝንም ይደምስስ በዘመናት ሁሉ የፀሐይና የጨረቃን ያኽል ረጅም ዘመናት ይኑር። ንጉሡ ሣሩ በታጨደ መስክ ላይ እንደሚዘንብ ዝናብ፥ በምድርም ላይ እንደሚወርድ ካፊያ ይሁን። በእርሱ ዘመን የጽድቅ ሥራ ይጠናከር፤ ጨረቃ ብርሃንዋን በምትሰጥበት ጊዜ ሁሉ ብልጽግና ይበርክት። ግዛቱ ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይድረስ። በምድረ በዳ የሚኖሩ በፊቱ ይስገዱ፤ ጠላቶቹም ወደ መሬት ወድቀው ትቢያ ይላሱ። የተርሴስ ደሴቶች ነገሥታት ስጦታ ያቅርቡለት፤ የሳባና የዐረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያምጡለት። ነገሥታት ሁሉ ይስገዱለት፤ ሕዝቦች ሁሉ ያገልግሉት። ወደ እርሱ የሚጮኹትን ድኾች፥ ችግረኞችንና የተጨቈኑትን ሰዎች ነጻ ያወጣል። ለድኾችና ለደካሞች ይራራል፤ በችግር ላይ ያሉትንም ሰዎች ከሞት ያድናል። የእነርሱ ሕይወት በእርሱ ዘንድ ውድ ስለ ሆነ ከጭቈናና ከዐመፅ ያድናቸዋል። ንጉሡ ረጅም ዘመን ይኑር! ከሳባ ወርቅ ይምጣለት፤ ስለ እርሱም ዘወትር ጸሎት ይደረግ፤ የእግዚአብሔርም በረከት ዘወትር ከእርሱ ጋር ይሁን! በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ፤ እንደ ሊባኖስ ተራራዎችም ፍሬያማ ይሁኑ፤ የእህሉም ነዶ እንደ ሣር የበዛ ይሁን። የንጉሡ ስም ለዘለዓለሙ ሲታወስ ይኑር፤ ዝናውም ፀሐይ በሚወጣበት ዘመን ሁሉ ይሰማ፤ ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ የተባረኩ ይሁኑ፤ እርሱንም “የተባረከ ነው!” ይሉታል። እርሱ ብቻ ተአምራትን የሚያደርገው፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! ክቡር ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! ክብሩ በምድር ሁሉ ይሙላ! አሜን! አሜን! የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎት እዚህ ላይ ተፈጸመ።
መዝሙር 72:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጥ፥ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥ ሕዝብህን በጽድቅ፥ ችግረኞችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ። በጽድቅ፥ ተራሮችና ኰረብቶች ለሕዝብህ ሰላምን ይቀበሉ። ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ይፍረድ፥ የድሆችንም ልጆች ያድን፥ ጨቋኙንም ይጨፍልቅ። ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥ በጨረቃም ፊት ለፊት ለልጅ ልጅ ይኑር። እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይውረድ። በዘመኑም ጽድቅ ያብብ፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ይብዛ። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይግዛ። በፊቱም የኢትዮጵያ ሰዎች ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፥ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ። ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል። ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፥ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፥ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፥ ደማቸው በፊቱ ክቡር ነው። በሐወት ይኑር፥ ከዓረብም ወርቅ ይሰጠው፥ ሁልጊዜም ስለ እርሱ ይጸልይ፥ ዘወትርም ይባረክ። በምድር ላይ እህሉ ይትረፍረፍ፥ በተራሮችም ላይ ሰብል ይወዛወዝ፥ ፍሬውም እንደ ሊባኖስ ከፍ ከፍ ይበል፥ ሰዎችም በከተማ እንደ ምድር ሣር ይለምልሙ። ስሙ ለዘለዓለም ይታወስ፥ እንደ ፀሐይ ዕድሜ ስሙ ጸንቶ ይኑር፥ የምድር አሕዛብ ሁሉ በርሱ ይባረኩ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመሰግኑት፥ ብቻውን ተኣምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ። የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘለዓለም ይባረክ፥ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። አሜን፥ አሜን። የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎቶች ተፈጸሙ።